ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች የአረንጓዴ ዓሻራ መርሃ ግብር አካሄዱ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች  የዘንድሮው የአረንጓዴ ዓሻራ መርሃ ግብር አካል የሆነውን የችግኝ ተከላ መርሃግብር አካሄዱ። 

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊ ስትራቲጂያዊ ጉዳዮች ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)  ጋር ውይይት ካካሄዱ በኋላ "የምትተክል ሀገር የሚያፀና ትውልድ" በሚል መሪ ሀሳብ የተጀመረው የዘንድሮው የአረንጓዴ ዓሻራ መርሃ ግብር አካል የሆነውን የችግኝ ተከላ አካሂደዋል።

ፓርቲዎች በሀሳብ የሚፎካከሩበትና በሀገራዊ ጉዳዮች በጋራ የሚሰሩት አዲስ የፖለቲካ ምእራፍ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ተከፍቷል።

በዚህም መነሻነት በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እየሰሩ ሲሆን ለአብነትም በዛሬው እለት በሱሉልታ ከተማ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር አካሂደዋል።


 

በሀገራችን የፖለቲካ ባህል እኩይ የሆነው በጠላትነት ተፈራርጆ ተቀራርቦ መስራት ነውር የሆነበት ጊዜ አልፎ ገዥው ፓርቲና የተፎካካሪ ፓርቲዎች በጠላትነት የሚተያዩበት ሁኔታ ተቀይሮ ለሀገር እና ለህዝብ በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት መጀመሩ ወደ ተሟላ የዴሞክራሲ ስርአት ለምናደርገው ጉዞ ተስፋ ሰጪ መሆኑ ተመላክቷል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህን ምእራፍ በማጠናከር የጋራ በሚያደርጓቸው ጉዳዮች በትብብር በመስራት፤ በሀሳብ በመፎካከር ኢትዮጵያን የመገንባት ኃላፊነታቸውን መወጣት መቀጠል እንዳለባቸው በመርሀ ግብሩ ላይ ጥሪ ቀርቧል።


 

በዴሞክራሲያዊ ፉክክር መንግስት ለመሆን የሚያሸንፈውም ሆነ በውድድሩ የሚፎካከሩ ፓርቲዎች ለአገር ልማት የበኩላቸውን ሚና የመወጣት ኃላፊነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።

በችግኝ ተከላ መርሃ-ግብሩ የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የአረንጓዴ ዓሻራ መርሃ ግብር ለአንድ አካል የሚተው ሳይሆን የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ትብብር የሚጠይቅ መሆኑን ገልፀዋል።

በቀጣይም በሀገራዊ የልማት መርሃ ግብሮች ላይ በትብብር እንደሚሰሩመረጋገጡም ከብልጽግና ፓርቲ ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም