ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት ቀናት በመኸር አምራች አካባቢዎች ለግብርና ስራ ምቹ የአየር ሁኔታ ይኖራል - የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/2016 (ኢዜአ)፦ በሚቀጥሉት አስር ቀናት የመኸር አምራችና የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ለግብርና ስራ ምቹ የአየር ሁኔታ እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳሳወቀው፣የቀጣዮቹ ቀናት የአየር ሁኔታ ለግብርና እንቅስቃሴ ጉልህ ሚና ይጫወታል።

የአየር ሁኔታው አስቀድመው ተዘርተው በተለያየ የዕድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ የመኽር ሰብሎች ዕድገትም ወሳኝ ነው ብሏል።

የመኽር እርሻን ዘግይተው ለሚጀምሩ አካባቢዎች የአፈር እርጥበትን በመጨመር ሰብሎችን በወቅቱ ለመዝራት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑንም ነው ኢንስቲትዩቱ በመግለጫው ያስታወቀው።

የአየር ሁኔታው ለቋሚ ተክሎች የውሃ ፍላጎትን ለማሟላት ለመጠጥና ለግጦሽ አቅርቦት መሻሻል የጎላ ሚና እንዳለውም ገልጿል።

በሌላ በኩል በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ከሚጠበቀው ከባድ ዝናብ ጋር ተያይዞ ቅጽበታዊ ጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችል አስጠንቅቋል።

በተከታታይ ዝናብ እያገኙ ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በሰብሎች፣ በእንሰሳትና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም