ቀጥታ፡

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የብዝኃ ህይወት መመናመንን በማስቀረት የስርዓተ ምህዳር ሚዛንን እያስጠበቀ ነው - የኢትዮጵያ ብዝኃ ህይወት ኢንስቲትዩት

 አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/2016(ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የብዝኃ ህይወት መመናመንን በማስቀረት ዘላቂ የስርዓተ ምህዳር ሚዛንን እያስጠበቀ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ብዝኃ ህይወት ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ስፋቷ 60 በመቶ በደን ኃብት የተሸፈነ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል። 

ይህ የደን ሽፋን በጊዜ ሂደት ወደ 40 በመቶ ከመቀነሱ ባለፈ በተደጋጋሚ የሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ክስተቶች ምክንያት ወደ 3 በመቶ መውረዱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

በዚህም የሀገር በቀል ዕጽዋትንና እንስሳትን ጨምሮ የብዝኃ ህይወት ሀብት መመናመንን ያስከተለ ሲሆን የስርዓተ ምህዳር መዛባትንም ፈጥሮ ቆይቷል።

የዓለም ፈተና የሆነው የአየር ንብረት ለውጥ ችግሩን አባብሶት የቆየ ሲሆን፥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ውጥን በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ቁልፍ መፍትሔ ሆኖ መጥቷል።

ባለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት ህዝብን በማስተባበር ከ32 ቢሊዮን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፥ ሀገር በቀል ዕጽዋትም ይገኙበታል።

በዚህም የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ማደጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የዘንድሮውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ባስጀመሩበት ወቅት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብዝኃ ህይወት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፈለቀ ወልደየስ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የብዝኃ ህይወት መመናመንን እያስቀረ ነው።


 

መርሐ ግብሩ በኢትዮጵያ በመጥፋት ላይ ለነበሩ ሀገር በቀል ዕጽዋት ትኩረት መስጠቱን ጠቅሰው፥ በዚህም በየዓመቱ በርካታ ችግኞች መተከላቸውን ነው ያብራሩት።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለብዝኃ ህይወት ጥበቃ ትልቅ እድል መሆኑን የገለጹት ፈለቀ(ዶ/ር)፤ ኢንስቲትዩቱም እየተመናመኑ ያሉ ዕጽዋትን ጠብቆ ለማቆየትና ለማባዛት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሀገር በቀል ዕጽዋትን መትከል የአካባቢ ስርዓተ ምህዳርን ሚዛን በዘላቂነት ከማስጠበቅ ባለፈ በመጥፋት ላይ ያሉ ዕጽዋቶች እንዲያገግሙ ሰፊ እገዛን እንደሚያደርግ አስረድተዋል።

ኢንስቲትዩቱ "የምትተክል ሀገር የሚያጸና ትውልድ" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ በሚገኘው የዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ እንደ ኮሶ፣ ብርብራ፣ የሀበሻ ጽድ፣ ቀርከሃና ሌሎች 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ሀገር በቀል ችግኞች ማዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ችግኞች በኢንስቲትዩቱ ስር ባሉ ዘጠኝ ማዕከላትና ለሌሎች ተቋማት ተደራሽ መደረጋቸውን አመላክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም በደቡብ ወሎ ዞን ሐይቅ ከተማ ባስጀመሩት የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ7 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ለመትከል ታቅዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም