ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በማደግ ላይ ያሉ አገራትን ታሳቢ ያደረገ ፍትኃዊ የፋይናንስ ሥርዓት ሊዘረጉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በማደግ ላይ ያሉ አገራትን ታሳቢ ያደረገ ፍትኃዊ የፋይናንስ ሥርዓት ሊዘረጉ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/2016(ኢዜአ)፦ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በማደግ ላይ ያሉ አገራትን ታሳቢ ያደረገ ፍትኃዊ የፋይናንስ ሥርዓት ሊዘረጉ እንደሚገባ የፋይናንስ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ጥሪ አቀረቡ።
አራተኛው የፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በዚሁ ጊዜ፤ በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሳቢያ ዓለም ባልተረጋጋ የፋይናንስ ሥርዓት ውስጥ ይገኛል ብለዋል።
ጎን ለጎንም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በማደግ ላይ ያሉ አገራት በዓለም ኢ-ፍትኃዊ የፋይናንስ ሥርዓት ምክንያት ችግር እየገጠማቸው መሆኑንም ነው ያስረዱት።
በመሆኑም ፍትኃዊ የፋይናንስ ሥርዓት በመዘርጋት የበለጸገች ዓለምን ለሁሉም ማዳረስ ይገባል ነው ያሉት።
ለዚህ ደግሞ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በማደግ ላይ ያሉ አገራትን ታሳቢ ያደረገ ወጥና ፍትኃዊ አሰራር መዘርጋት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ በበኩላቸው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጋረጠው የፋይናንስ ችግር ለመፍታት እንደዚህ አይነት ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ወሳኝ ናቸው ብለዋል።
ድርቅ፣ ጉርፍ፣ ግጭትና ኮቪድ 19 ችግሩን አባብሶታል ያሉት ሚኒስትሩ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ለመቀነስ ቀጣይነት ያለው ሥራ መሥራት ይገባል ብለዋል።
የአዲስ አበባ አክሽን አጀንዳና አጀንዳ 2030 ለማሳካት ቀጣይነት ያለው የልማት ግቦችን በበቂ ፋይናንስ መደገፍ ይገባል ብለዋል።
ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት አካታች ሪፎርም ሊያደርጉ እንደሚገባ ገልጸው፣ ሕገ-ወጥ የፋይናንስ ዝውውርን በጋራ መግታት ይገባል ብለዋል።
ለአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በቂ ፋይናንስ ማቅረብና ትብብርና ቁርጠኝነትን ማሳደግ የቀጣይ የቤት ሥራ ሊሆን እንደሚገባ አብራርተዋል።
በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው ጉባኤ በቀጣይ የፈረንጆች ዓመት በስፔን ከሚካሄደው 4ኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ አስቀድሞ የተዘጋጀ መድረክ ነው።