የአራተኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 15/2016(ኢዜአ)፦የአራተኛው ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

በመርሀ ግብሩ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሀመድ እና ሌሎች ታዳሚዎች ተገኝተዋል።

የዛሬው ኮንፍረንስ እ.አ.አ ከሰኔ 30 እስከ ሐምሌ 3/2025 በስፔን ለሚካሄደው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባኤ የተዘጋጀ የቅድመ ጉባኤ መድረክ ነው።

የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ባስተላለፉት መልዕክት በዓለም ላይ በጂኦ ፖለቲካ ልዩነት ላይ የተመሰረተ ኢ-ፍትሐዊ የፋይናንስ ፍሰት ችግር ተፈጥሯል ብለዋል።


 

በቀጣይ ዓመት የሚደረገው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ጉባኤ ይህን የተዛባ የፋይናንስ ስርዓት መስመር እንደሚያስይዝ እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በስፔን የሚካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ንግድና ኢንቨስትመንትን በማጠናከር  የተሳለጠ የፋይናንስ ስርዓት ለመዘርጋት የጎላ አበርክቶ ይኖረዋል ነው ያሉት ዋና ፀሐፊው።

እ.አ.አ በ2015 በአዲስ አበባ በተዘጋጀው ሶስተኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ኮንፍረንስ ለጸደቀው የውሳኔ ሀሳብ (Addis Ababa Action Agenda, Resolution 69/313) እና ለ2030 የዘላቂ ልማት ግቦች መሳካት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሊኖር እንደሚገባም አሳስበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም