ቀጥታ፡

በባህር ዳር ከተማ ከ230 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ኢንተርፕራይዞች ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ተሸጋገሩ

ባህር ዳር  ፤ሀምሌ 14/2016 (ኢዜአ)፦በባህር ዳር ከተማ ከ230 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 16 ኢንተርፕራይዞች ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ መሸጋገራቸውን የከተማው ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታወቀ።

የከተማ አስተዳደሩ የ2016 በጀት ዓመት ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ ደረጃ ለተሸጋገሩ ኢንተርፕራይዞች የእውቅና አሰጣጥ መርሃ ግብር መድረክ በባህር ዳር ተካሄዷል።


 

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የባህር ዳር ከተማ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ብርሃን ንጉሴ እንደገለጹት፤ በኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን በመፍታት የማምረት አቅም እንዲሻሻል እየተሰራ ነው።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ተመርቶ ለውጭ ገበያ ከቀረበ ምርት 18 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት መቻሉን ጠቅሰው፤ ተኪ ምርቶችን በራስ አቅም በማምረት ከ25 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማዳን እንደተቻለም ገልፀዋል።

በበጀት ዓመቱ 27 የአምራች ኢንዱስትሪዎች እንደ አዲስ ምርት እንዲጀምሩ በማድረግ ለአንድ ሺህ 547 ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለ ተናግረዋል።

አምራች ኢንተርፕራይዞችን ካሉበት ወደ ቀጣዩ የኢንዱስትሪ ደረጃ እንዲሸጋገሩ ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰው፤ በዚህም 16 ኢንተርፕራይዞች ባስመዘገቡት ተጨባጭ ውጤት ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ መሸጋገር ችለዋል ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው እንደገለጹት፤ የባህር ዳር ከተማን ለነዋሪዎቿና ለጎብኚዎች ምቹ፣ ውብና ጽዱ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የኢንዱስትሪ መዳረሻ ከተማ እንድትሆን የሚያስችሉ ተግባራት በትኩረት እየተሰሩ ነው።


 

የከተማዋን እምቅ የመልማት ፀጋ በመለየት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር አበረታች ውጤት እየታየ መሆኑን አስረድተዋል።

አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚያስገኙት ጥቅም ዘርፈ ብዙ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢንዱስትሪዎችን በሙያና በአመራር የመደገፍ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ የተሸጋገሩት ኢንተርፕራይዞች በቀጣይ ለሚያከናውኑት የኢንዱስትሪ ስራ የመሬት አቅርቦትን ጨምሮ አስፈላጊ የድጋፍና ክትትል ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልፀዋል።

ከተሸጋገሩት ኢንተርፕራይዞች መካከል የኤፍሬም፣ ዮሐንስና ጓደኞቻቸው የምግብ ግብዓት አቅርቦት የህብረት ሽርክና ማህበር ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ወጣት ኤፍሬም ውቤ እንደገለጸው፤ እዚህ ደረጃ ለመድረስ ከራስ ጥረት በተጨማሪ የከተማ አስተዳደሩ ክትትልና ድጋፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው።


 

ማህበሩ ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ የተሸጋገረው ካፒታሉን 21 ሚሊዮን ብር ላይ በማድረሱ መሆኑን ጠቅሶ፤ ከ50 በላይ ለሚሆኑ ወገኖች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ፈጥሮ እያሰራ እንደሚገኝ ተናግሯል።

ለዩኒቨርሲቲዎች የምግብ ግብዓቶችን እያቀረቡ መሆኑን የገለፀው ወጣት ኤፍሬም በቀጣይ ማህበሩ አገልግሎቱን ወደ ውጭ ሀገር የማስፋት ዕቅድ ይዞ እየሰራ እንደሆነም አመልክቷል።

በከተማ አስተዳደሩ 206 ኢንዲስትሪዎች በማምረት ሂደት ላይ እንደሚገኙ በመርሃ ግብሩ ላይ የተጠቀሰ ሲሆን በዕውቅና አሰጣጥ ስነ ስርዓቱ ላይም የከተማው አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ መሆናቸውም ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም