ቀጥታ፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ የውይይት መድረኮች የዳበረ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት ጥሩ መሰረት የሚያኖር ነው- የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 14/2016 (ኢዜአ)፦ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ የውይይት መድረኮች ሀገራዊ ችግሮችን በጋራ ለመፍታትና የዳበረ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት ጥሩ መሰረት የሚያኖር መሆኑን የፖለቲካ ፖርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት በወቅታዊና ዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አድርገዋል።

በመድረኩ ላይ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃን ጨምሮ ሌሎችም አመራሮችና የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ተገኝተዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃ፤ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የመነጋገር ባህልን በማጎልበት ሀገራዊ ችግሮችን በጋራ የመፍታት ልምድ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየት መንግስት እያሳየ ያለውን ቁርጠኝነት አድንቀው፤ ፓርቲዎችም ለዚሁ ዝግጁ መሆን አለባቸው ሲሉ ተናግረዋል። 

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ የውይይት መድረኮች ሀገራዊ ችግሮችን በጋራ ለመፍታትና የዳበረ የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት ጥሩ መሰረት የሚያኖር መሆኑንም ገልጸዋል።

የዛሬው መድረክ ዓላማም በፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ የሚፈቱትን በጋራ ለመፍታት የሚያስችል ውይይት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለህዝብና ለትውልድ ተስፋ የሚሆኑ ዓላማዎችን በመሰነቅ ኢትዮጵያን ከችግር ለማውጣት በጋራ ልንቆምና ልንሰራ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።


 

በብልፅግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ባሕል ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ እና የጋራ ምክር ቤቱ ስራ አስፈፃሚ አባል መለስ ዓለሙ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የመመካከር ሂደት አዲስ የፖለቲካ ባህል ጅማሮ መሆኑን ገልጸዋል።

በመነጋገር ሀገራዊ ጥቅሞችን ማስጠበቅ፣ ችግሮችን መፍታትና መልካም ነገሮችን ማስቀጠል የሚቻል መሆኑን ተናግረዋል።

ሀገር እየመራ ያለው ብልጽግና ፓርቲ የዳበረ የዴሞክራሲ ስርአት ለመገንባት በጽናትና በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም