በኦሮሚያ ክልል በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት መስኮች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተግባራት ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት መስኮች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተግባራት ተከናውነዋል
አዳማ፤ ሐምሌ 14/2016(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት መስኮች የህዝቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተግባራት መከናወናቸውን ከጨፌው አባለት ለተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ የክልሉ ሴክተሮች የአመራር አባላት ገለፁ ።
የጨፌ ኦሮሚያ 7ኛ መደበኛ ጉባዔ በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በጉባዔው በአገልግሎት አሰጣጥና መልካም አስተዳደር፣ የልማት ፕሮጀክቶችን አስመልክቶ በተለይም በጤና፣ በውሃ፣ ትምህርት፣ በመንገድ እንዲሁም በሰላምና ፀጥታ ዙሪያ ከጨፌ አባላት የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተዋል።
ለአስተያየቶቹና ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ከሰጡት መካከል የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መንግሥቱ በቀለ አንዱ ናቸው።
ዶክተር መንግሥቱ በምላሻቸው እንደገለፁት የጤና መሰረተ ልማትን ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ በህክምና መሳሪያዎችና በመድኃኒት አቅርቦት እንዲሁም የዘርፉን ተቋማት አቅም በማሳደግ ረገድ የተሻለ ስራ ተሰርቷል።
"መልካ በሎ፣ ሆሮ ጉዱሩና ሀሬሮ የጤና ተቋማት ግንባታን ለማጠናቀቅ እየሰራን ነው" ያሉት ዶክተር መንግስቱ፤ በቦረና፣ በሁለቱ ጉጂና በባሌ ሆስፒታሎች ሲቲ ስካንና ኤም አር አይ ማሽኖችን ለማስገባት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የመድኃኒት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት 500 የህዝብ መድኃኒት ቤቶች መደራጀታቸውን ጠቅሰው፤ በመድሃኒት አቅርቦት ዙሪያ ችግር የፈጠሩ ለ1ሺህ 501 ግለሰቦች ማስጠንቀቂያ መሰጠቱንና 738 በሚሆኑት ላይ ደግሞ የቅጣት እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።
በተመሳሳይ 50 የመድሃኒት ንግድ ፍቃዶች መሰረዛቸውን አመልክተዋል።
በክልሉ የወባ በሽታ ስርጭት ለመግታት ህዝቡን ያሳተፉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አንስተው፤ 7 ነጥብ 2 ሚሊዮን አጎበር መሰራጨቱን ለአብነት አንስተዋል።
በተመሳሳይ በንፁህ መጠጥ ውሃ በበጀት ዓመቱ በመንግሥትና በህዝብ ተሳትፎ የተሰሩት 9 ሺህ 600 ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ህዝብ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ኢንጅነር አራርሶ አብዱለጢፍ ገልጸዋል።
ነጆ፣ ኒኦ ገሰራ፣ ሳሚራ ኮልባ፣ ግንዲሪ፣ ጊምቢቹ ፈንታሌን ጨምሮ ስድስት ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በአዲሱ በጀት ዓመት ትኩረት መሰጠቱን በማከል።
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሳደግ ትኩረት መደረጉን የገለፁት ደግሞ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ ናቸው።
በተለይም በመጀመሪያና 2ኛ ደረጃ የመማሪያ መጻሕፍት ተደራሽ በማድረግ አበረታች ስራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም የ2ኛ ደረጃ መጻሕፍት ተደራሽ ማድረግ ችለናል ነው ያሉት።
15ሺህ መምህራን የአቅም ግንባታና ደረጃቸውን ለማሻሻል በስልጠና ላይ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
የተማሪዎች ምገባን ለማሳደግና ጥራቱን የማሻሻል ስራም ቀጣይ ትኩረት የተሰጣቸው ናቸው ብለዋል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በበኩላቸው በክልሉ በልማት ኢንሼቲቮች ቀድሞ ያልተለመዱ የሩዝና ሌሎች ሰብሎችን ጨምሮ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ የተሰሩ ሥራዎች ውጤት ተገኝቶባቸዋል ብለዋል።
በተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ረገድም በተለይም በአሁኑ የመኸር እርሻው አርሶ አደሩ ከዝግጅት ጀምሮ እስከ አጠቃቀሙ ድረስ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ በበኩላቸው በክልሉ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈንና ልማትን ለማስቀጠል በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
በዚህም በክልሉ በሰፈነው ሰላም የክልሉን ገቢ ከማሳደግ ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚሰጡ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ ማስመረቅ ተችሏል ነው ያሉት።
ህዝቡ በተደራጀ መልኩ የአካባቢውና የክልሉን ሰላም እንዲጠበቅ በተከናወነው ተግባርም አበረታች ውጤት ተገኝቷል ነው ያሉት።
ለተነሱት አስተያየቶችና ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ በበኩላቸው፤ ክልሉ ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ 20ሺህ 664 የልማት ፕሮጀክቶችን በመንግስትና በህዝብ አቅም ገንብቶ በበጀት ዓመቱ ለአገልግሎት ማብቃቱን ተናግረዋል።
ህዝቡ በልማቱ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖረውና ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ፣ የክልሉን ልማት በራስ አቅም ለመሸፈን የዞኖችና ከተሞች ገቢን ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎችም አመርቂ ውጤት መገኘቱን አመልክተዋል።
በዜግነት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ በባህላዊ ፍርድ ቤቶችና በቡሳ ጎኖፋ የመረዳዳት ሥርዓት የተሰሩ ስራዎች ውጤት የተገኘባቸውና ተጠናክረው የሚቀጥሉ ናቸው ብለዋል።