በአትሚስ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሶማሊያ ለቤይ ሆስፒታል የህክምና ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በአትሚስ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሶማሊያ ለቤይ ሆስፒታል የህክምና ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ ሐምሌ 14/2016(ኢዜአ)፦ – በአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ(አትሚስ) በሶማሊያ በማገልገል ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ለማሻሻል የህክምና ቁሳቁሶችን ለቤይ ሆስፒታል ድጋፍ ማድረጉን የአፍሪካ ህብረት በይን መረብ ዘገበ።
የአፍሪካ ህብረት በይን መረብ ዘገባ ዛሬ እንዳስታወቀው የቤይ ክልል ሆስፒታል በደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ግዛት ውስጥ የሚገኝ የጤና ተቋም ነው።
ሰራዊቱ የህክምናቁሳቁሶች ድጋፉን ያደረገው ከደቡብ ምእራብ ክልል አስተዳደር በቀረበለት ጥያቄ መሰረት የተሰጠ ምላሽ መሆኑ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከተለገሱት የህክምና ቁሳቁሶች መካከል 73 ልዩ ልዩ መድሃኒቶች እና አንቲባዮቲኮች ሎሌች አስፈላጊ ቁሳቁሶችንም ያካተተ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል።
በተጨማሪም የቀዶ ህክምና እርዳታ መስጫ ቁሳቁሶችን ሰራዊቱ ለሆስፒታሉ መለገሱን አብራርቷል።
በባይዶዋ የሚገኘው የአትሚስ ደረጃ ሁለት ሆስፒታል ኃላፊ ዶክተር ተረፈ ንጉሴ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በተበረከቱት የተለያዩ የህክምና ቁሳቁስ አቅርቦቶች የአካባቢውን ህዝብ አስቸኳይ የጤና ክብካቤና አገልገሎት ፍላጎቶች እንደሚያሟሉ እና እንደሚያሻሽሉ ተናግረዋል ።
የኤቲኤምአይኤስ ቀጣይነት ያለው የህክምና ጥረት የሚደነቅ ነው ያሉት ዶክተር ንጉሴ፤ ድጋፉ በኤቲኤምአይኤስ ደረጃ ሁለት ለበለጠ ህክምና ለሚፈልጉ ወይም ለልዩ ህክምና ለሚላኩ ነዋሪዎች የሆስፒታሉ ሀኪሞች በየሳምንቱ የሚሰጡትን የነጻ ህክምና አገልግሎቶችንም አንደሚያግዝ አስረድተዋል።
በደቡብ ምዕራብ ግዛት አስተዳደር ስም ልገሳውን የተቀበሉት የባይደዋ ከተማ ከንቲባ አብዱላሂ ዋቲን የመከላከያ ሰራዊቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ የሚያበረክተውን ሁለንተናዊ ድጋፍ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
በአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ በሶማሊያ ማህበረሰቡን ለመርዳት ወደግዛቲቱ ስለመጡም ምስጋና አቅርበው፤ “ችግር ገጥሞን በጠራናቸው ቁጥር ሁልጊዜም ለጥያቄዎቻችን ፈጣን ምላሽ ይሰጡናል ” ሲሉ ከንቲባ ዋትን መናገራቸውም ተገልጿል።
የሆስፒታሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲፈታ ኢብራሂም ሃሺ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ከኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሰራዊት የተገኘውን የእርዳታ ድጋፍ የአካባቢውን ህብረተሰብ በተለይም ደግሞ አቅመ ደካሞችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
አቶ አብዲፈታ ኢብራሂም ሃሺ አክለውም “ልገሳው የተገኘው ሆስፒታሉ አስፈላጊ የሆኑ የህክምና አቅርቦቶች ባለቀበት ወቅት በመሆኑ ሰራዊቱ የሰጠው ምላሽ የሚያስመሰግን ነው” ሲሉም ጠቅሰዋል።
አብዲፈታ አክለውም የህክምና ቁሳቁሰ እጥረቱ በታካሚዎች ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ከፍተኛ መሆኑንን አንስተዋል።
በ1936 የተመሰረተው የቤይ ክልል ሆስፒታል በባይዶዋ ከተማ እምብርት ላይ የሚገኝ የህዝብ ጤና ተቋም ሲሆን፤ በደቡብ ምዕራብ ግዛት የቤይ እና ባኮልን ነዋሪዎች እንዲሁም በአጎራባች የጁባላንድ ግዛት የጌዲኦ ክልል ነዋሪዎችን ያገለግላል።
ሆስፒታሉ የቀዶ ጥገና፣ የእናቶች ክብካቤ፣ የህፃናት ጤና ክብካቤ፣ የተመጣጠነ ምግብ፣ የተመላላሽ ታካሚ ህክምና እና የላብራቶሪ አገልግሎቶችን ጨምሮ ነፃ የጤና አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑም ተጠቅሷል።
በደቡብ ምዕራብ ግዛት አስተዳደር በዓለም አቀፍ አጋሮች ድጋፍ የሚተዳደረው ይኸው ተቋም በክልሉ የጤና አጠባበቅ ስርዓት ውስጥ ወሳኝ ሚና እንዳለውም ዘገባው አመልክቷል።