የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ በተጓዳኝ በማኅበራዊ አገልግሎትም ላይ በስፋት እየተሳተፍን ነው - ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ በተጓዳኝ በማኅበራዊ አገልግሎትም ላይ በስፋት እየተሳተፍን ነው - ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ በተጓዳኝ በማኅበራዊ አገልግሎትም ላይ ሰራዊቱ በስፋት እየተሳተፈ መሆኑን የኮማንዶና አየር ወለድ እዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ ገለጹ።
የኮማንዶና አየር ወለድ እዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማን ጨምሮ ሌሎች የእዙ ከፍተኛ መኮንኖችና አባላት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሆኑት መካከል የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ እና በሸገር ከተማ የኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ የጤና ኬላ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ አኑረዋል።
ሌተናል ጄኔራል ሹማ በዚሁ መርሃ-ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር፤ እዙ የኢትዮጵያን ሰላም እንዲጠበቅ ልማቷ እንዳይቆም የህይወት መስዋዕትነት ከፍሎ ለዛሬ ያደረሰ ነው።
የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ በተጓዳኝ በማኅበራዊ አገልግሎትም ላይ ሰራዊቱ በስፋት እየተሳተፈ መሆኑን ገልፀዋል።
ከዚህ ቀደም በደም ልገሳ፣ በአረንጓዴ አሻራ ልማትና ሌሎችም መስኮች ተሳትፎ መደረጉን አስታውሰው፤ ቀጣይነት የሚኖረው መሆኑን አረጋግጠዋል።
በዛሬው እለት የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠለት የጤና ኬላ ግንባታም ከክረምት የበጎ ፈቃድ ሥራዎች መካከል አንዱ መሆኑን ገልፀዋል።
የሚገነባው የጤና ኬላም ሠራዊቱ ከደመወዙ አዋጥቶ የሚሰራው እና በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ እንደሚያስረክብ ጠቁመዋል።
በሸገር ከተማ የኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ አስተዳዳሪ ፍቃዱ ቱሉ፤ የኮማንዶና አየር ወለድ አባላት የሀገርን ክብርና ሉዓላዊነት ከማስጠበቅ ባለፈ ለበጎ ተግባራቸው አድንቀው ምስጋናቸውንም አቅርበዋል።
በመርሃ-ግብሩ እዙ እያስገነባ ያለውን ዋና መምሪያ ጠቅላላ የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።