ቀጥታ፡

የመዲናዋን ወጣቶች በማሳተፍ በርካታ የበጎ ፍቃድ ተግባራትን እያከናወንን ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 14/2016(ኢዜአ)፦ የመዲናዋን ወጣቶችና የስፖርት ቤተሰብ በማሳተፍ በርካታ የበጎ ፍቃድ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ገለጸ።

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ "የምትተክል ሀገር ፤ የሚያፀና ትውልድ "በሚል መሪ ቃል  የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር  በእንጦጦ ፓርክ አከናውኗል ። 

በመርሃ ግብሩ የተገኙት የቢሮው  ሃላፊ አቶ በላይ ደጀን ቢሮው የመዲናዋን ወጣቶችና የስፖርት ቤተሰቦች በማሳተፍ በርካታ የበጎ ፍቃድ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በከተማ አስተዳደሩ 17 ሚሊየን ችግኞች  እንደሚተከሉ አንስተዋል ፡፡ 

ከዚህ ውስጥ 30 ሺህ ችግኞች በወጣቶችና ስፖርት ቢሮ እንዲተከሉ በከተማ አስተዳደሩ መሰጠቱን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም በዛሬ ዕለት በከተማው ከሚገኙ 11 ክፍለ ከተሞች የተወጣጡ ወጣቶች ፣ የስፖርት ቤተሰቦች፣ አንጋፋና ታዋቂ አትሌቶች፣ የስፖርት ክለብ ደጋፊዎች እና በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች በእንጦጦ ፓርክ በመገኘት 20 ሺህ ችግኝ መትከላቸውን አስታውቀዋል ፡፡


 

በዘንድሮ ዓመት እንደ ሀገር በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የተያዘው ውጥን ግቡን እንዲመታ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ አሳስበዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ እግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አንዷለም ጌታቸዉ ውብና ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር በተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ተሳታፊ በመሆኑ መደሰቱን ተናግረዋል ፡፡

ጽዱ አካባቢን መፍጠርና ንጹህ አየር ማግኘት ለቀጣይ ትውልድም የሚጠቅም በመሆኑ የተጀመረው የችግኝ ተከላ ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል ብለዋል  ፡፡

ወጣት አቶ አብዱ ለጃ በበኩሉ ችግኝ መትከል ለሀገር ጠቃሚ መሆኑን በመገንዘብ በየዓመቱ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ተሳታፊ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

ችግኝ ከመትከል ባለፈ የሚተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ልምድ እንዳለው በመግለጽ ሁሉም ችግኝ ከመትከል ባለፈ መንከባከብን ልማድ ማድረግ አለበት ብሏል ፡፡

በዘንድሮ የክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ 2 ሚሊየን በላይ ወጣቶች እና ስፖርት ቤተሰቦች በ14 የበጎ ፍቃድ ተግባራት ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ አክለዋል ፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም