ቀጥታ፡

ሌተናል ጄነራል ሹማ አብደታ ለኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ የጤና ኬላ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 14/2016(ኢዜአ)፦የኮማንዶና አየር ወለድ እዝ አዛዥ ሌተናል ጄነራል ሹማ አብደታ፤ ለኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ የማህበረሰብ አገልግሎት የሚውል የጤና ኬላ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አስቀመጡ።

ሌተናል ጄነራል ሹማ በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር፤ እዙ የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት ከማስጠበቅ በተጓዳኝ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራ ላይ በስፋት እየተሳተፈ መሆኑን ገልጸዋል።

በዛሬው እለት የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የጤና ኬላ ግንባታም ከክረምት የበጎ ፈቃድ ስራዎቻችን መካከል ነው ብለዋል።

ከዚህ ቀደም በደም ልገሳ፣ የአረንጓዴ አሻራ ልማትና ሌሎችም መስኮች ተሳትፎ መደረጉን አስታውሰው ቀጣይነት የሚኖረው መሆኑን አረጋግጠዋል።

የሚገነባው የጤና ኬላም ሰራዊቱ ከደመወዙ አዋጥቶ የሚሰራው እና በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ እንደሚያስረክብ ጠቁመዋል።

በሸገር ከተማ የኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ አስተዳዳሪ ፍቃዱ ቱሉ፤ የኮማንዶና አየር ወለድ አባላት የሀገርን ክብርና ሉአላዊነት ከማስጠበቅ ባለፈ ለበጎ ተግባራቸው አድንቀው ምስጋናቸውንም አቅርበዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ሌተናል ጄነራል ሹማን ጨምሮ ሌሎች የእዙ ከፍተኛ መኮንኖችና አባላት ታድመዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም