በበጎ ፍቃድ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት ለመጪው ዓመት የሚያግዘንን በቂ ዕውቀት እያገኘን ነው- ተማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በበጎ ፍቃድ የክረምት ማጠናከሪያ ትምህርት ለመጪው ዓመት የሚያግዘንን በቂ ዕውቀት እያገኘን ነው- ተማሪዎች

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 14/2016(ኢዜአ)፦በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በሚሰጠው የማጠናከሪያ ትምህርት ለመጪው ዓመት የሚያግዘንን በቂ ዕውቀት እያገኘን ነው ሲሉ ተማሪዎች ገለጹ።
የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በራሱ ለነገ አገር ተረካቢዎች መሰረት የሚጥሉ በጎነትን ፣ መረዳዳትን ፣ የአገር ፍቅርን ለማስተማር የማይተካ አበርክቶ አለው፡፡
በራስ በጎ ፍቃድ የሚከናወኑ ሰብዓዊ ተግባራት ታዳጊዎች በመልካም ስብዕና እንዲታነፁ ፣ያላቸውን ሌሎች እንዲያካፍሉ ፣የተቸገሩ ወገኖችን እንዲደግፉና በፍቅርና በመልካም ስነ ምግባር ተኮትኩተው አገራቸውን እንዲያገለግሉ ያግዛሉ፡፡
በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ካሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች መካከል የክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት አንዱ ሲሆን ከሀምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በመዲናዋ በሚገኙ ከ200 በላይ ትምህርት ቤቶች በመሰጠት ላይ ይገኛል።
ኢዜአ በደጃዝማች ሃይሉ ተስፋዬ እና በፀሐይ ጮራ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመገኘት በክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት በመማር ላይ የሚገኙ ተማሪዎችን አነጋግሯል ፡፡
በደጃዝማች ሃይሉ ተስፋዬ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የማጠናከሪያ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት ተማሪ ኪሩብል ወንደሰንና ተማሪ ረድኤት አበበ በዕድሉ በመጠቀም ጥሩ እውቀት እያገኘን ነው በማለት ተናግረዋል፡፡
የሚሰጠው ትምህርት በተለይም በመጪው ዓመት ለሚወስዱት የስድስተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በእጅጉ እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል።
በፀሐይ ጮራ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆነችው ተማሪ ኤልሻዳይ ደሳለኝ በበኩሏ፤ የክረምት ትምህርት መማሯ የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደሚያግዛት ትገልጻለች፡፡
በደጃዝማች ሃይሉ ተስፋዬና በፀሐይ ጮራ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ መምህራን በበኩላቸው በበጎ ፈቃደኝነት የማይከፈል ዋጋ የሚያስገኝ መልካም ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በደጃዝማች ሃይሉ ተስፋዬ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲያተስምር ያገኘነው በጎ ፈቃደኛ መምህር በሃይሉ ስሜ ላለፉት ስድስት አመታት በበጎ ተግባሩ መሳተፉን በመግለጽ ፤ የነገ አገር ተረካቢ በሆኑ ትውልዶች ላይ አሻራውን ማስቀመጥ ትልቁ አላማው እንደሆነ ነው የገለጸው ፡፡
በፀሐይ ጮራ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በጎ ፈቃደኛ መምህር ተስፋዬ ቦዳ በበኩሉ፤ በበጎ ፈቃድ ስራ ለረጅም ጊዜ መሳተፉን ገልጾ እውቀቱን ለትውልዱ በማካፈሉ ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል።
በተለይም ተማሪዎች ከትምህርት ባሻገር በስነ ምግባር የታነጹ እንዲሆኑ እየሰሩ እንደሆነና የክረምት ትምህርት ተማሪዎች እውቀታቸውን እንዲያጎለብቱ ጥሩ መሰረት እየጣለ መሆኑን ተናግሯል።
በአዲስ አበባ የኅብረተሰብ ተሳትፎና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አብርሃም ታደሰ ፤በመዲናዋ ከግንቦት 18 ጀምሮ 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ወጣቶችን በማሳተፍ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በመዲናዋ 2 ሺህ በሚሆኑ በጎ ፈቃደኞች አማካኝነት ለ35 ሺህ የአንደኛ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የክረምት የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ እንደሚገኝም ጠቁመዋል ።