በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ20 ሺህ በላይ ቤቶችን ለአቅመ ደካማና አረጋዊያን ሰርቶ ለማስረከብ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ20 ሺህ በላይ ቤቶችን ለአቅመ ደካማና አረጋዊያን ሰርቶ ለማስረከብ እየተሰራ ነው
ሶዶ፣ ሐምሌ 13/2016(ኢዜአ) በብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር ከ20 ሺህ በላይ ቤቶችን ለአቅመ ደካሞችና ለአረጋዊያን ሰርቶ ለማስረከብ አቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን አስታወቀ።
የብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ሊግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጽህፈት ቤት "በጎነት ለእህትማማችነት፣ ለትውልድ ግንባታና ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ የክረምት በጎ ፈቃድ ማጠናከሪያ መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ አካሂዷል።
የሊጉ ሥራ አስፈጻሚ አባል ወይዘሮ ህሊና መብራቱ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ሊጉ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራትን እያከናወነ ነው።
ከነዚህ መካከል በመላ አገሪቱ ከ20ሺህ በላይ የአቅመ ደካሞችና አረጋዊያን ቤት ግንባታና እድሳትን ጨምሮ የደም ልገሳ፣ የሴቶች የማህፀን ጫፍ ካንሰር ምርመራ ማድረግን ያካትታል።
እንዲሁም ወላጆቻቸው የመግዛት አቅም ለሚያንሳቸው ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላትና የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ማከናወን ሌሎቹ ተግባራት መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅትም ደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን ጨምሮ በአራት ክልሎች ላይ የአቅመ ደካሞችና አረጋውያን ቤት ግንባታና እድሳት ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል።
በቀጣይ ሣምንት ደግሞ በሌሎች ሦስት ክልሎች ላይ ተመሳሳይ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ይጀመራሉ ብለዋል።
ሊጉ ወላጆቻቸው የመግዛት አቅም ለሚያንሳቸው ተማሪዎች ሁለት ሚሊዮን ደብተር ለማሰራጨትና 500 ሺህ ሴቶችን የማህፀን ጫፍ ካንሰር ምርመራ እንዲያደርጉ ማቀዱንም ወይዘሮ ህሊና አስታውቀዋል።
የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ የደቡብ ኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ እቴነሽ በየነ፤ ሊጉ በክልሉ የአባላቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም በዛሬው እለት በወላይታ ሶዶ ከተማ የሁለት አቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሥራ መጀመሩን ነው የተናገሩት።
በሶዶ ዙሪያ ወረዳ የኮካቴ ቀበሌ ላይም በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ውጤታማ የሆኑ ሴቶችን የመጎብኘትና የማበረታታት ሥራ ማከናወናቸውን አመልክተዋል።
ይህም ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር በሚደረገው ጥረት የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማጎልበት ጉልህ ሚና አለው ነው ያሉት።
በአገልግሎቱ የቤት ግንባታ የተጀመረላቸው በወላይታ ሶዶ ከተማ የአራዳ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ፐለሄ ሱንታ ለተደረገላቸው ድጋፍ ሊጉን አመስግነዋል።
ወቅቱ ክረምት ከመሆኑና ቤታቸው ከማርጀቱ ጋር ተያይዞ ኑሯቸውን ቢያከብደውም፤ አሮጌው ቤታቸው ፈርሶ በምትኩ አዲስ ቤት ግንባታ በመጀመሩ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል።
የሊጉ ከፍተኛ አመራር አባላት በወላይታ ሶዶ ከተማ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አከናውነዋል።