ቀጥታ፡

የፅንፈኛው ቡድን የሎጂስቲክስ አቅራቢውን ጨምሮ አዲስ ሲሰለጥኑ የነበሩ አባላቱ በቁጥጥር ሥር ዋሉ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/2016(ኢዜአ)፦የፅንፈኛው ቡድን የሎጂስቲክስ አቅራቢውን ጨምሮ አዲስ ሲሰለጥኑ የነበሩ አባላቱ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

በደቡብ ወሎ ዞን አምባሳል ወረዳ ለሚንቀሰቀሰው ፅንፈኛ ቡድን ሎጂስቲክ አቅራቢ የነበረው ነጋ ፋንታሁንን ጨምሮ አዲስ ሰልጣኝ የቡድኑ አባላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ የኮማንዶ ሬጅመንት አዛዥ ሻለቃ ታሪኩ ሻሜቦ ገልፀዋል።

ለፅንፈኛው ሃይል ድሽቃ ለመግዛት ያሠበው ነጋ ፋንታሁን የተባለው ግለሰብ ከራያ ቆቦ መነሻውን በማድረግ ወደ ደሴ በመምጣት 01 ድሽቃ በ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ለመግዛት ተስማምተው ዲሽቃውን ጭኖ ከደሴ ከተማ በመውጣት ላይ እያለ በሬጅመንቷ የመረጃ ክፍል አባላት በቁጥጥር ሥር ውሏል።

መነሻቸውን አዲስ አበባና ግሸን ደብረ ከርቤ በማድረግ ለእኩይ አላማቸው የተሰበሰቡና ስልጠና ሲወስዱ የነበሩ ሰልጣኞችና አሰልጣኞችን ጨምሮ በአርጎባ ማህበረሰብ ቃሉ ወረደ ድማ ቀበሌ ላይ እያሉ ከነግብረ አበሮቻቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል።

እነዚህን አባላት በቁጥጥር ስር በማዋል በተሰራው ስራ የቃሉ ወረዳ የፅንፈኛው ቡድን ሃላፊ የነበረውን አብዱ መሃመድን ጨምሮ 16 የፅንፈኛው ሰልጣኞችን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል ።

የህዝቡን ሠላም ለማደፍረስና የሠላሙ መረጋጋት እንዳይቀጥል ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ የቡድኑ አባላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሬጅመንቷ አዛዥ ተናግረዋል ።

በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ግለሠቦች መካከል ነጋ ፋንታሁን የተባለው ድሽቃ ገዥ እኔ እዚህ እናንተጋ ተይዤ ከመምጣቴ በፊት ስለ እናንተ የምንሠማው ነገር እጅግ የሚያሥፈራ ነበር እናንተጋ የመጣ እንደሚገደል ነበር የሚነግሩን አሁን ግን እዚህ መጥተን የምናየው ነገር ከሚነገረን ነገር ጋራ በምንም አይገናኝም ብሏል።

በተመሣሣይ የቡድኑ አሠልጣኝ ኤፍሬም አባተም እኛ ወጣቱን በማደራጀት በህዝብና በመንግሥት ያለውን የሠላማዊ ግንኙነት ለማደፍረሥ ነበር እቅዳችን ይህን አሥከፊ ድርጊት ብናስበውም አልተሣካልንም ብሏል።

በእናንተ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በኮማንዶ ተይዘን እዚህ ከመጣን በኋላ የምናየው ነገር ሁሉ እዛ እንደሚነገረን አይደለም የሚነገረን ምግብ አይሠጧችሁም ይገድሏችኋል ይሉ ነበር ግን ሀሰት ነው ሲል ተናግሯል።

እኛ እስከ አሁን በጣም በተሣሣተ መንገድ የሕዝቡን ሠላም ስንረብሽ ቆይተናል አሁን ግን በፈፀምነው የሽብር ስራ ተፀፅተናል ከዚህ በኋላ ከመንግሥት ጎን በመቆም ለሠላም እንሠራለን ሲሉም በፀፀት ገልፀዋል።

የሬጅመንቷ አዛዥ ሻለቃ ታሪኩ ሻሜቦ እስከ አሁን በደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች የኮማንዶ ሬጅመንቷ በሰራችው አኩሪ ግዳጅ እስከ አሁን ለከተማ ሽብር ተግባር የተላኩትን 106 የፅንፈኛው አባላትን በቁጥጥር ስር በማዋል የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉን ተናግረዋል።

ህገ-ወጥ የዶላር ዝውውር በጥቁር ገበያ የሚነግዱ አባላትንም ጭምር በህግ ቁጥጥር ስር በማዋል በተሰራው ስራ እስከ አሁን 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ከጥቁር ገበያ ወደ መንግስት ካዝና እንዲገባ ተደርጓል ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም