ቀጥታ፡

የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን በማሳደግ የአርብቶ አደሩን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል 

ዶሎ ፤ሐምሌ 13/2016(ኢዜአ)፡-በገጠራማ ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን በማሳደግ የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሡልጣን ወሊ (ዶ/ር) አስታወቁ።

በሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን ዳራቶሌ ወረዳ በ90 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ የፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀከት ዛሬ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

ፕሮጀክቱ ከ7ሺህ በላይ ለሚሆን የአርብቶ አደር ማህበረሰብና ለተለያዩ ተቋማት አገልግሎት እንደሚሰጥ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ ተገልጿል።

ሚኒስትር ዴኤታው ፕሮጀክቱን በመረቁበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የአርብቶ አደር ቀበሌዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የፀሐይ ሃይል ኤሌክትሪክ ተደራሽ በማድረግ የማህበረሰቡን ሕይወት በመሠረታዊነት ለመለወጥ እየተሰራ ነው።

ከዋና የኤሌክትሪክ ማሰራጫዎች ርቀው በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች እየተሰፋፉ የሚገኙት የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች አርብቶ አደሮች ዘመናዊ አኗኗርን በመከተል ከእንስሳት ሃብታቸው ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኙ እንደሚረዳ ጠቁመዋል።


 

"አርብቶ አደሩ ለዘመናዊ ኑሮ ቅርብ ነው፤ ኤሌክትሪክ ማግኘቱ በተንቀሳቃሽ ስልኩ መረጃ በመለዋወጥ ሃብቱን በአግባቡ ለመጠቀም ያግዘዋል" ብለዋል።

በተጨማሪም አርብቶ አደሩን ወደ ከፊል አርሶ አደርነት ለማሸጋገር በሚደረገው እንቅስቃሴ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የውሃ መሳቢያ ሞተሮች ጥቅም ላይ በማዋል ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚያግዙም ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል።

የሶማሌ ክልል የማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ኤድመን መሐመድ በበኩላቸው፤ በአካባቢው አገልግሎት መስጠት የጀመረው የኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት የማህበረሰቡን አኗኗር በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀይረው ገልጸዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች በፕሮጀክቱ የተገነባው የሃይል ማመንጫ ጣቢያ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጥ ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያደርጉለትም አሳስበዋል።

የዳራቶሌ ወረዳ የአገር ሽማግሌው አቶ አህመድ አደይስ በበኩላቸው እንዳሉት ፤ ወረዳው የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ መሆኑ የአርብቶ አደሩ ህይወትና የልጆቻቸውን ቀጣይ ኑሮ በከፍተኛ ደረጃ ይለውጣል።

"ለፕሮጀክቱ አስፈላጊውን ጥበቃና ክትትል እናደርጋለን፤  እንደ ዓይናችን ብሌን እንጠብቀዋለን።" ብለዋል።

''የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ በተለይ ልጆቻችን ጥሩ ትምህርት አግኝተው የተሻለ ደረጃ እንዲደርሱ ያግዛል'' ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ነኢሞ መሐመድ  የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ናቸው።

በፕሮጀክቱ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላት፣ የአገር ሽማግሌዎች እና የወረዳው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም