በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ አካባቢ ግዙፍ የሲሚንቶ ፋብሪካ ሊገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ አካባቢ ግዙፍ የሲሚንቶ ፋብሪካ ሊገነባ ነው
መቀሌ፤ ሐምሌ 13/ 2016(ኢዜአ)፡- በትግራይ ክልል ከመቀሌ ከተማ አካባቢ 18 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በሆነ ወጪ ግዙፍ የሲሚንቶ ማምረቻ ፋብሪካ ሊገነባ መሆኑ ተገለጸ።
የፕሮጀክቱ ባለቤት "ተጎጋ " የተሰኘው አገር በቀል የሲሚንቶ ፋብሪካ አክሲዮን ማህበር ሲሆን፤ ማህበሩ ግንባታውን በተቋራጭነት ከሚያከናውነው "ሳይኖማ" ኢንተርናሽናል ኢንጅነሪንግ ከተባለ የቻይና ኩባንያ ጋር ዛሬ የውል ስምምነት ተፈራርሟል።
ማህበሩ ስምምነቱን የተፈራረመው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኔቴናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ በተገኙበት ነው።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሌተናል ጄኔራል ታደሰ ወረደ በስምምነት ፊርማው ስነ-ስርዓት ላይ እንደገለጹት፤ የሲሚንቶ ግብዓት ለልማት ግንባታ ስራዎች መፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።
ሊዚህም ፋብሪካው በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ግንባታው ተጠናቆ ምርቱን ለአገራችን ብሎም ለምስራቅ አፍሪካ እንዲያቀርብ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የ"ተጎጋ" ሲሚንቶ ማምረቻ ፋብሪካ ቦርድ ሰብሰቢ አቶ አሸናፊ ሃይለ እንዳስታወቁት፤ ፋብሪካው በ18 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወጪ ይገነባል።
በ100 ሄክታር ቦታ ላይ የሚገነባው የሲሚንቶ ፋብሪካው ከሶስት ዓመታት በኋላ ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባ በዓመት እስከ ሁለት ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም እንደሚኖረው በጥናት መረጋገጡን ገልጸዋል።
ሥራ ሲጀምር አንድ ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች ቋሚ የሥራ እድል እንደሚፈጥርም አቶ አሸናፊ ተናግረዋል።
ከመቀሌ ከተማ በስተምዕራብ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ "ተጎጋ" በተሰኘው መንደር የሚገነባው ሲሚንቶ ፋብሪካው በአካባቢው ለ75 ዓመታት የሚያገለግል የሲሚንቶ የጥሬ ሃብት እንዳለው በባለሙያዎች ጥናት መረጋገጡን አስታውቀዋል።
አገራችን ብቻ ሳይሆን ለምስራቅ አፍሪካ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ መስፋፋት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ተገልጿል።
የ"ሰይኖማን " ኢንተርናሽናል ኢንጅነሪንግ ኩባንያ የኢትዮጵያ ተወካይ ሚስተር ዩሊያንግ ብረይት በበኩላቸው፤ ኩባንያው በኢትዮጵያ ካሉ ግዙፍ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች መካከል አንዱ የሚሆነው የተጎጋ ሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ ከዳር ለማድረስ ሁለንተናዊ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።