ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በመኸር የግብርና ወቅት ከ60 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል

ሶዶ ሐምሌ 13/2016 (ኢዜአ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በመኸር ወቅት ከሚከናወነው የግብርና ልማት ሥራ ከ60 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ መንግሥት ዋና ተጠሪ በክልሉ መሬት ጾም እንዳያድርና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራ አሳስበዋል። 

“ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ ለብልጽግና ራዕይ ስኬት” በሚል መሪ ቃል ክልል አቀፍ የመኸር ግብርና ንቅናቄ መድረክ ዛሬ በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሂዷል።

በዚህን ወቅት የቢሮው ሃላፊ አቶ ሃይለማሪያም ተስፋዬ እንዳሉት በክልሉ በመኸር የግብርና ወቅት 769 ሺህ 724 ሄክታር መሬት በማረስ ከ60 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ነው።


 

የቅድመ ምርትና የድህረ ምርት ቴክሎሎጂዎችን በአግባቡ በመጠቀም ምርታማነትን ለመጨመርና የምርት ብክነት ለመቀነስ ልዩ ትኩረት መሰጠቱንም ገልጸዋል።

የግብርናው ዘርፍ በምግብ ራስን ከማስቻል ባለፈ ለኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ በመሆን ብሎም የውጭ ምንዛሬና የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ያለው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በክልሉ 70 በመቶ ያህል መሬት ያለ ቴክኖሎጂ የሚመረትበት መሆኑን ያመለከቱት አቶ ሃይለማሪያም፣ ይህን ለመቀየር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በተለይም የግብርናውን ዘርፍ ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ፣ በቴክሎጂ በመደገፍ እንዲሁም በገበያ ላይ ተፈላጊ ምርቶችን ለማግኘት ሁሉም መዋቅር የድርሻውን እንዲወጣ ይደረጋል ነው ያሉት።

በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ከ1 ሺህ 900 በላይ የዓሣ፣ የዶሮ፣ የወተት፣ የሥጋና የንብ እርባታ መንደሮች መቋቋማቸውንና የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት ማደጉን ገልጸው፣ በአዲሱ የበጀት ዓመት ለዘርፉ ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።

በክልሉ በመኸር የግብርና የልማት ወቅት ምርታማነትን ማሳደግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሰራ ያሳሰቡት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ዓለማየሁ ባውዲ ናቸው።


 

ለዚህም በየአካባቢው መሬት ጾም እንዳያድርና የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ክፍተቶችን በማረም ግቡን ለማሳካት ርብርብ እንዲደረግ አስገንዝበዋል።

ክልሉ ያለውን አቅምና ዕድል በመጠቀም ከተረጂነት ለመላቀቅና ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህንን በተጨባጭ ለማሳካት ሁሉም ትጋትና ጥረት የታከለበት እንቅስቃሴ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል። 

ገበያን ለማረጋጋትና ምርታማትን ለመጨመር የተጀመረውን ጥረት ለማጠናከር ያሉንን ፀጋዎች በአግባቡ ለመጠቀም ይሰራል ያሉት ደግሞ የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ፎላ ናቸው።


 

በዞኑ የመኸር ግብርናን ውጤታማ ለማድረግና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን  ለማረጋገጥ የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ከማሳደግ በተጨማሪ ክትትልና ድጋፍን ለማጠናከር እንደሚሰራ ገልጸዋል። 

የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር ለምግብ ዋስትና፣ ለገቢ፣ ለሥራ ዕድል ያለው አስተዋጽኦ የጎላ በመሆኑ በበጀት ዓመቱ ከመኸር ግብርና ጎን ለጎን ትኩረት እንደሚሰጠው አመልክተዋል።

በመድረኩ ላይ የክልሉና የዞን ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ የወረዳ ዋና አስተዳዳሪዎችና የመንግሥት ተጠሪዎች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም