ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን በማፍራት ዜጎች ተጠቃሚ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን በማፍራት ዜጎች ተጠቃሚ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/2016(ኢዜአ)፦የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን በማፍራት ዜጎች ተጠቃሚ የማድረግ ተግባሩን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ ተናገሩ።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር በዘርፉ በተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎችና በተገኙ ውጤቶች ላይ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ በትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ፤ በጥቃቅን አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ረቂቅ ፖሊሲና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ምክክር ተደርጓል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ፤ የበለፀገ ማኅበረሰብና አገር ለመገንባት የትምህርትና ሥልጠና ዘርፉ የማይተካ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
የክህሎት ሥልጠና በልዩ ልዩ መስኮች ዜጎች ውጤታማ ሆነው ለአገራቸው ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የሚያስችል መሆኑንም ነው ያነሱት።
ይህንን ተከትሎ ሚኒስቴሩ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ሥራ ሥምሪት ተወዳዳሪ ባለሙያ በማፍራት ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የጀመረው ሥራ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ዜጎች እንደፀጋዎቻቸው ወደ ሥራ እንዲገቡና ተኪ ምርቶችን እንዲያመርቱ፤ ከዚህም ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ እንዲሆን አመርቂ ሥራ ተሰርቷል ነው ያሉት።
ሚኒስቴሩ የሥራ ዕድል በመፍጠር ብቻ ሳይሆን ሥነ-ምህዳሩንም ምቹ ከማድረግ እንዲሁም ሠላማዊ ኢንዱስትሪ ከመፍጠር አኳያ የሚያበረታታ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ሚኒስቴሩ ያስመዘገባቸውን አበረታች ውጤቶች ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
ምክር ቤቱም ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚሁ ጊዜ፤ ባለፉት ዓመታት በክህሎት ልማት፣ ሥራ ዕድልና ሰላማዊ ኢንዱስትሪ ለመፍጠር በተሰራው ሥራ ተጨባጭ ውጤቶች ተገኝተዋል ብለዋል።
ጎን ለጎንም የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ለማጠናከር፣ በኢንዱስትሪዎች ፍላጎት መሰረት የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት፣ ዜጎችን በማሰልጠን በውጭ አገር የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ውጤታማ ሥራ መሰራቱን አብራርተዋል።
በቀጣይም ሚኒስቴሩ ያለፉትን ዓመታት ልምዱን በመቀመር በአዲስ እሳቤ የተለያዩ ተግባራት ለማከናወን ማቀዱን ገልጸው በዋነኝነት የክህሎት ልማትን በፍላጎት መር አጫጭር ሥልጠና ላይ መሰረት በማድረግ በስፋት ለመስጠት መታቀዱን ተናግረዋል።
በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ወደ ተሟላ የዲጂታል አሰራር ለማሸጋገርና በራሳቸው አቅም የሚተዳደሩ ነጻ ተቋማትን ለመገንባት መታቀዱን ይፋ አድርገዋል።
በአሁን ወቅት የዲጂታል አሰራሩን በ100 ፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጆች ለመተግበር አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅሰው ከእነዚህ ውስጥ 86ቱ በተለያየ ደረጃ አሰራሩን እየተገበሩ መሆኑን አስረድተዋል።
በተጓዳኝም፤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሁም በአካባቢዎች የሚገኙ ፀጋዎችን ታሳቢ ያደረጉና በእሴት ሰንሰለት ላይ የተመሠረቱ ሥልጠናዎች እንዲሰጡም ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።
የክህሎት ልማት፣ የሥራ ዕድልና ሠላማዊ ኢንዱስትሪ የመፍጠር ሥራዎች የሁሉንም አካላት ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑ የጠቆሙት ሚኒስትሯ ምክር ቤቱም ይህንን ከግምት በማስገባት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።