ጫካ ፕሮጀክት አዲስ አበባን ማራኪ ገጽታ የሚያላብስና ኢትዮጵያን በበጎ መልኩ የሚያስተዋውቅ ነው - ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን - ኢዜአ አማርኛ
ጫካ ፕሮጀክት አዲስ አበባን ማራኪ ገጽታ የሚያላብስና ኢትዮጵያን በበጎ መልኩ የሚያስተዋውቅ ነው - ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/2016(ኢዜአ)፦ጫካ ፕሮጀክት አዲስ አበባን ማራኪ ገጽታ የሚያላብስና ኢትዮጵያን በበጎ መልኩ የሚያስተዋውቅ ነው ሲሉ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ተናገሩ።
ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ታዳጊዎች በጫካ ፕሮጀክት አረንጓዴ አሻራቸውን ያሳረፉ ሲሆን፤ በፕሮጀክቱ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎችንም ጎብኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ታህሳስ 13 ቀን 2016 ዓ.ም በውጭ ሀገራት የተወለዱ ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎም ከዚህ ቀደም በሁለት ዙር የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገር ቤት መጥተው በተለያዩ ተግባራት ተሳትፈዋል።
አሁን ደግሞ በሶስተኛ ዙር በርካታ ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው የመጡ ሲሆን፤
በዛሬው እለትም የሁለተኛ ትውልድ ታዳጊዎች የጫካ ፕሮጀክትን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ከተሳተፉት መካከል ከአሜሪካ የመጣው ታዳጊ ኢዮሲያስ ዓለማየሁ፤ ፕሮጀክቱ እጅግ ውብና የሚያስደስት መሆኑን ተናግሯል።
በፕሮጀክቱ እየተከናወኑ ያሉ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ለአዲስ አበባ ከተማ የተለየ ውብትና ድምቀት እንደሚሆኑም ነው የጠቆመው።
የሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን አባላትም ወደ ሀገራቸው መጥተው ፕሮጀክቱን መጎብኝት እንዳለባቸውም ገልጿል።
ሌላኛዋ ከአሜሪካ የመጣችው ታዳጊ ኣመኒ አሊ፤ ፕሮጀክቱ እጅግ ውብ መሆኑን ገልጻ፤ ይህም ሰዎች ከተለያዩ አገራት ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ እድል የሚፈጥር ነው ብላለች።
የፕሮጀክቱ ተፈጥሯዊ ገጽታ የተለየ የደስታ ስሜት እንደሚፈጥርም ነው የተናገረችው።
ከጀርመን የመጣችው ታደጊ ኩሽማ አሊ መሀመድ፤ በኢትዮጵያ ቆይታዋ ብዝሃ ባህሎችና ማንነቶች መኖራቸውን እንደተገነዘበች ጥቅሳ፤ ይህም እጅግ ደስ እንዳሰኛት ተናግራለች።
በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም ለአካባቢ መጠበቅ ተግባራዊ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ተናግራለች።
ጫካ ፕሮጀክት እጅግ ማራኪ ገጽታ እንዳለው ጠቅሳ፤ ፕሮጀክቱ ለአዲስ አበባ አዲስ ገጽታ የሚሰጥና ነዋሪዎችም መዲናዋን በተለየ አቅጣጫ እንዲመለከቱ የሚያደርግ ነው ብላለች።
ሁለተኛ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን ጫካ ፕሮጀክትን በመጎብኘት የኢትዮጵያን ማራኪ ገጽታ እንዲገነዘቡ ጥሪ ያቀረበው ደግሞ ከአሜሪካ የመጣው ታዳጊ ናትናኤል ሃብታሙ ነው።