ኮርፖሬሽኑ በ2016 በጀት ዓመት በገቢ እድገት እና በመፈጸም አቅም ግንባታ ረገድ ከፍተኛ ስኬት አስመዝግቧል - ኢዜአ አማርኛ
ኮርፖሬሽኑ በ2016 በጀት ዓመት በገቢ እድገት እና በመፈጸም አቅም ግንባታ ረገድ ከፍተኛ ስኬት አስመዝግቧል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/2016(ኢዜአ)፦ የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በተገባደደው በጀት ዓመት በስድስት የሪፎርም ዓመታት በተለይ በገቢ እድገት እና በመፈጸም አቅም ግንባታ ረገድ ከፍተኛ ስኬት ማስመዝገቡን አስታወቀ፡፡
ኮርፖሬሽኑ በ2016 በጀት ዓመት የእቅድ አፈፃፀም እና በ2017 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ውይይት አድርጓል፡፡
በዚህም በ2016 በጀት ዓመት የኮርፖሬሽኑ ዓመታዊ ገቢ 4 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ሆኖ መመዝገቡን ከኮርፖሬሽኑ ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ተቋማዊ ሪፎርም ሲጀምር ከነበረበት 2010 ዓ.ም ተመሳሳይ በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ13 እጥፍ የገቢ እድገት ማሳየቱም በመረጃው ተጠቁሟል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት አካል በሆኑ የኮርፖሬሽኑ ሕንጻዎችና ይዞታዎች ላይ የሪኢኖቬሽንና የማስዋብ ሥራ በመስራት የድርሻውን መወጣት የሚያስችል አቅም መፍጠሩ ጠንካራ የመፈጸም አቅም ማሳያ እንደሆነም ተመላክቷል፡፡
ግንባታቸው የተጠናቀቁ ሕንጻዎችን ወደ አገልግሎት እንዲገቡ መደረጉንና በመጠናቀቅ ላይ የሚገኙ የግንባታ ሳይቶችን ደግሞ የማጠናቀቂያ ስራዎች በፍጥነት እየተከናወኑ መሆኑም በመድረኩ ተገልጿል፡፡
በከተሞች የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት ችግር መቅረፍ የሚያስችል የተለያዩ የማህበረሰብ አካላትን ተሳታፊ የሚያደርጉ መርሀ ግብሮችን መንደፉንም ተጠቁሟል፡፡
መርሀ ግብሮቹን ተግባራዊ ለማድረግ የፋይናንስ አቅሙን ማጠናከር የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑም በመድረኩ ተጠቅሷል፡፡
በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ከሚገኙ አቻ ተቋማት ጋር በትብብር መስራት የሚያስችሉ ሥራዎች መሰራታቸውም በስኬት መገምገሙ ተገልጿል፡፡
ከዚህ በፊት ሲሰጥ የነበረውን የአገልግሎት አሰጣጥ በማሻሻል፣ ደንበኞች የአገልግሎት ክፍያቸውን በቀላሉ በእጅ ስልካቸው ተጠቅመው በ4 የተለያዩ ባንኮችን እና በቴሌብር እፈየፈጸሙ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከሰማንያ ስድስት በላይ ህንፃዎችን በማደስ የከተማዋን ስታንዳርድ እንዲያሟሉና ውብ ገጽታ እንዲላበሱ ማድረግ መቻሉም በመድረኩ ተነስቷል፡፡
የግንባታ ግብዓት እጥረትን ማቃለል የሚያስችሉ ብሎም እንደሀገር ተጨማሪ አቅም መሆን የሚችል የአርማታ ውህድና ብሎኬት ማምረቻ ማዕከልን በዚሁ በጀት ዓመት ተከላውን በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉም ተገልጿል፡፡
ኮርፖሬሽኑ የ2017 በጀት ዓመት እቅድ ላይም ውይይት ያደረገ ሲሆን ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች እና ዓብይ ተግባራት ላይ ተጨማሪ የትግበራ አቅጣጫ በስማቀመጥ ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የነበረውን ውይይት ማጠናቀቁም በመረጃው ተመላክቷል፡፡