የታዳጊዎች የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሥልጠና የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን የሚያደርጉ ወጣቶችን ለማፍራት መሰረት የሚጥል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የታዳጊዎች የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሥልጠና የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን የሚያደርጉ ወጣቶችን ለማፍራት መሰረት የሚጥል ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/2016(ኢዜአ)፦የሰው ሰራሽ አስተውሎት የክረምት የታዳጊዎች ሥልጠና የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ የሚችሉ ወጣቶችን ለማፍራት መሰረት እየጣለ መሆኑን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡
የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሶስተኛው ዙር የታዳጊዎች የክረምት ስልጠና ማስጀመሪያ መርኃ ግብር በሳይንስ ሙዚየም ተከናውኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገትና የኢኮኖሚ ሽግግር አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የማይተካ ሚና እንዳለው በመግለጽ በዘርፉ ላይ መስራት እንደሚገባ በተለያዩ መድረኮች ማንሳታቸው ይታወሳል።
በተለይም ለመጭው ዘመን ትውልድ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በታዳጊዎችና ወጣቶች ላይ መልካም ዘር መዝራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ተነጥላ መቀመጥ እንደማትችልና በዘርፉ እየተከናወነ ያለው ስራ አበረታች መሆኑንም መጠቆማቸው አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) በስልጠናው ማስጀመሪያ መርሐግብር ላይ እንዳሉት፤ ለዘንድሮው ስልጠና ከ3 ሺህ በላይ ታዳጊዎች ተመዝግበው 200ዎቹ ተመርጠዋል።
በዓለም ላይ በፍጥነት እያደገ የመጣውን የሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚመጥን የሰው ሀይል ለማፍራት በታዳጊዎች ላይ መስራት ይገባል ብለዋል።
ለዚህም ኢንስቲትዩቱ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ምርምር በማድረግ የሀገራቸውን ችግር የሚፈቱና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን መስራት የሚችሉ ታዳጊዎችን እያሰለጠነ መሆኑን ገልጸዋል።
ስልጠናው ችግር ፈቺ ምርምር በማድረግ በዘርፉ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያጎለብቱ ወጣቶችን ለማፍራት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ገልጸው፤ የክረምት ሰልጣኝ ታዳጊዎች ችግር ፈቺ ፕሮጀክቶችን ማፍለቅ እንዲችሉ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርሜሽን ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህርት ማርታ ይፍሩ (ዶ/ር)፤ በዚህ ዘመን ቴክኖሎጂ በእያንዳንዱ ቤት በቀላሉ የሚገኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቴክኖሎጂ ተስፋም ስጋትም እንዳለው ገልጸው፤ ወጣቶች በእጃቸው ላይ ያለውን ቴክኖሎጂ በአግባቡ በመጠቀም ለሀገር ልማትና እድገት ሊያውሉት ይገባል ብለዋል፡፡
የቴክኖሎጂ ባለሙያው ሰለሞን ሙሉጌታ ካሳ፤ ሰው ሰራሽ አስተውሎት የሀገሪቱን ችግር የሚፈታ፣ ህይወትን የሚያቀል ቴክኖሎጂ መሆኑን ገልጿል፡፡
ሰው ሰራሽ አስተውሎት የዲጅታል ዘመን መዘውር፣ ታላቅ የቴክኖሎጂ አብዮት በመሆኑ ታዳጊዎች በጥንቃቄ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
በመጀመሪያው እና በሁለተኛው ዙር የክረምት የታዳጊዎች ስልጠና ሰልጣኞች ተማሪ ይዲዲያ ታደሰ እና ዮሴፍ ልዑልሰገድ፤ በወሰዱት ስልጠና የቴክኖሎጂ አቅማቸውን ማሳደጋቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ኢንስቲትዩቱ በሰጣቸው ፕሮጀክት መሰረት ዘመናዊ የአይነ ስውራን ዘንግ እና ማንነታቸው ያልታወቀ ሰዎች ወደ ቤት ሲገቡ በእጅ ስልክ ምልክት የሚሰጥ የደህንነት መጠበቂያ ቴክኖሎጂ አበልጽገው ሥራ ላይ ማዋላቸውን ተናግረዋል፡፡