ከዛሬ ፈተና የነገ ተስፋ ገዝፎ የሚታያቸው ባለ ራዕይ ተማሪዎች

በርካታ ታዳጊዎች ገና በልጅነት ዕድሜያቸው ብዙ የህይወት ፈተና ለመጋፈጥ የሚገደዱባቸው የህይወት አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ።

አንዳንዶች በፈተናዎቹ በመረታት ህልማቸው ሲጨነግፍ ሌሎች ደግሞ ከትናንት ፈተናዎቻቸው በመማር፣ ዛሬን በጥንካሬ በመኖር እና ነገን ተስፋ በማድረግ በህይወታቸው ለውጥ ሲያመጡ ይስተዋላል።

ሳምራዊት ሲሳይ፣ ምህረት ባዬ፣ አብርሃም ግዛቸው እና ኤፍሬም ሲሳይ ብዙ የሚያመሳስሏቸው ነገሮች አሉ።

ተማሪዎቹ ገና በልጅነት ዕድሜያቸው በግብአት እጥረት ትምህርት ለማቋረጥ እስከመገደድ እንዲሁም ቤተሰብን ለማገዝ የመኖሪያ ቀዬን ጥሎ ወደ ከተማ እስከመኮብለል የደረሰ የህይወት ፈተና ተጋፍጠዋል። 

ነገር ግን ለፈተናዎች ባለመረታት ዓመታትን ወደፊት አሻግረው በመመልከት የነገ የህይወት መንገዳቸውን በየራሳቸው አማራጭ እያበጁ መሆኑም ያመሳስላቸዋል።   

ሳምራዊት ሲሳይ የ16 ዓመት ታዳጊ ስትሆን ትውልዷና እድገቷ አዲስ አበባ ነው። 

ሳምራዊት በእውቀት ለፍሬ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ9ኛ ክፍል ትምህርቷን አጠናቃ በክረምት ወራት ለ10ኛ ክፍል የሚሆናትን ዝግጅት ከወዲሁ እያደረገች ትገኛለች።

ትምህርት የሰው የሕይወት መስመር ነው የምትለው ሳምራዊት ወደፊት አዋላጅ ሀኪም በመሆን ሀገሯን የማገልገል ሕልም አላት።


 

ሌላኛዋ ባለ ሩቅ ህልም ታዳጊ ምህረት ባዬ ትውልዷ መቀሌ ሲሆን በልጅነቷ ወደ አዲስ አበበ መጥታ ትምህርቷን በሻምፒዮንስ አካዳሚ በመከታተል ላይ ትገኛለች። 

በጣም ጎበዝና የደረጃ ተማሪ ስትሆን በ8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና በከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ወደ 9ኛ ክፍል አልፋለች።

መሐንዲስ (ኢንጂነር) የመሆን ራዕይ ያላት ታዳጊዋ እናትና አባቶቻችን ያስረከቡንን ሀገር እኔና አሁን ያለው ትውልድ ከዚህ በተሻለ ሁኔታ ለማሳደግ አደራ አለብን ብላለች።


 

በጅማ ከተማ የተወለደውና በልጅነት እድሜው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ኑሮን ለብቻው መግፋት የጀመረው አብርሃም ግዛቸው ትምህርትን የሕይወቱ ለውጥ ቁልፍ መሳሪያ በማድረግ በትጋት እየተማረ 10ኛ ክፍል ደርሷል።

በምህንድስና ሙያ አገሩን ማገልገልን በማለም ዛሬ ላይ ነገውን እየሰራ ይገኛል።

ገና በልጅነት እድሜው ኑሮን ለማሸነፍና ቤተሰቡን ለመደገፍ ከወሎ ወደ አዲስ አበባ እንደመጣ የሚናገረው ወጣት ኤፍሬም ሲሳይም በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ተመርቆ ኢትዮጵያን በሙያው የማገለልገል ሕልም አለው።

ተማሪዎቹ ከራሳቸው አልፈው በክረምት ወራት ሌሎችን በበጎ ፈቃድ እያስተማሩና እያገዙ ይገኛሉ።

እነዚህ ታዳጊዎችና ወጣቶች በፈተናዎች ሳይረቱ ትምህርታቸው ላይ በማተኮር የወደፊት ራዕያቸውን ዛሬ ላይ መቅረጽ ለመጀመራቸው ዋነኛ ምክንያቱ የውስጥ ብርታትና ጥንካሬያቸው እንደሆነ ይናገራሉ።

ዛሬ ላይ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በማሸነፍ የተሻለ ነገ እንደሚመጣ በማመን በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውስጥ ‘Sustainable East African Education and Development Society’ (ሲድስ) የተሰኘው የበጎ አድራጎት ድርጅት በተለያየ መንገድ እየደገፋቸው መሆኑንም ያነሳሉ።


 

የድርጅቱ የጋራ መስራች ምህረት ወርቁ ድርጅቱ በአሁኑ ሰዓት ለ160 የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች የትምህርት ግብዓቶችና ሌሎችን ቁሳቁሶችን በመደገፍ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ውጤታማ እንዲሆኑ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ዋንኛ ግቡ የነገ አገር ተረካቢ የሆኑ ተማሪዎች በዘላቂነት ተቋቁመው ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ መሆኑን አመልክተዋል።

የሲድስ ድርጅት የኢትዮጵያ አስተባባሪ ዓለም ዘለቀ ድርጅቱ ለተማሪዎች የጤና መድህን በመክፈልና ለወላጆች የመነሻ ገንዘብ በመስጠት ራሳቸውን እንዲያቋቁሙ እየደገፈ መሆኑን ገልጸዋል።


 

አብዛኞቹ ተማሪዎች በሚደረግላቸው ድጋፍ በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት እያስመዘገቡ ነው ያሉት አስተባባሪዋ የተሻለ የትምህርት ደረጃ ላይ የደረሱ ተማሪዎች በመልካም ፈቃደኝነት ለተማሪዎች የትምህርት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።

የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችና ተቋማት በሕጻናት ትምህርት ላይ በመስራት ልጆች በችግር ምክንያት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ የሴቶች፣ ሕጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ይታይሽ ደነቀው ሲድስ በክፍለ ከተማው ወረዳ 1 ቆሼ እየተባለ በሚጠራው ስፍራ የሚገኙ ልጆችና ወላጆችን በመደገፍ ተማሪዎች በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ድርጅቱ የድጋፍ አድማሱን በማስፋት እንዲሁም ተማሪዎችና ወላጆች ከተረጂነት ተላቀው በዘላቂነት ሊቋቋሙ በሚችሉባቸው ሁኔታ ላይ ይበልጥ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።


 

የክፍለ ከተማው የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ክትትልና ግምገማ ባለሙያ መስከረም ሙለታ ድርጅቱ ድጋፍ የሚያደርግላቸው ተማሪዎች በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን ገልጸዋል።

ትምህርት ለሕይወት ትልቅ መሰረት በመሆኑ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ለዘርፉ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም