የሆስፒታሉ ማስፋፊያ የክልሉን የሜዲካል ቱሪዝም የሚያጎለብት ነው- አቶ ኦርዲን በድሪ - ኢዜአ አማርኛ
የሆስፒታሉ ማስፋፊያ የክልሉን የሜዲካል ቱሪዝም የሚያጎለብት ነው- አቶ ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/2016(ኢዜአ) በሐረሪ ክልል እየተገነባ ያለው የፌደራል ፖሊስ ሆስፒታል ማስፋፊያ ፕሮጀክት የክልሉን የሜዲካል ቱሪዝም ይበልጥ የሚያጎለብት ነው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በሀረሪ ክልል እየተገነባ የሚገኘውን የፌደራል ፖሊስ ሆስፒታል ማስፋፊያ ፕሮጀክትን ተመልክተዋል።
በመስክ ምልከታውም እንደተገለፀው ሆስፒታሉ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስን ጨምሮ የአጎራባች ክልሎች የፖሊስ አባላት እና ቤተሰቦች እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብ በቅርበት አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው።
በክልሉ ለጤና ኮሪደር ልማት እና የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ልዩ ትኩረት ተሰቶት ወደ ስራ መገባቱን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ የሆስፒታሉ ማስፋፊያ በክልሉ በጤና ዘርፍ የሚሰጠውን አገልግሎት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ የራሱን አስተዋፆ የሚያበረክት መሆኑን ገልፀዋል።
በተለይ ሀረር ከአጎራባች ክልሎች ለህክምና የሚመጡ በርካታ ተገልጋዮች የሚስተናገዱባት የሜዲካል ቱሪዝም ከተማ መሆኗን በማመላከት የሆስፒታሉ ማስፋፊያ የሜዲካል ቱሪዝሙን ይበልጥ የሚያጎለብት ነው ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ጥሩ በሚባል አፈፃፀም ላይ እንደሚገኝ በማመላከት ፕሮጀክቱ በፍጥነት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንዲችል የክልሉ መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግም ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል።