በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የምናደርገው ተሳትፎ ተጠናክሮ ይቀጥላል - የኃይማኖት አባቶች - ኢዜአ አማርኛ
በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የምናደርገው ተሳትፎ ተጠናክሮ ይቀጥላል - የኃይማኖት አባቶች
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/2016(ኢዜአ)፦ በአረንጓዴ አሻራ ልማት መስኩ የተያዙ ሀገራዊ ግቦች እንዲሳኩ የኃይማኖት አባቶች በመርኃ ግብሩ የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለጹ።
የአዲስ አበባ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የ2016 ዓ.ም አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርኃ ግብርን ዛሬ ጀምሯል።
ጉባኤው ከተለያዩ የኃይማኖት ተቋማት የተውጣጡ የእምነት አባቶችን ያሳተፈ የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር አካሂዷል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ተወካይ መላከ ጸሀይ ቆሞስ አባ ወልደ ገብርኤል እንደተናገሩት፤ የኃይማኖት አባቶች ከጸሎትና ምዕመናን በሥነ-ምግባር ከመግራት ጎን ለጎን አረንጓዴ አሻራና መሰል የልማት ሥራዎች ላይ መሳተፍ አለባቸው።
በዚህም ለምዕመኑ አርአያ መሆን አለብን ያሉት አባ ወልደ ገብርኤል በአንድነት ለበጎ ዓላማ መሰለፍ አለብን ብለዋል።
ዛሬ ከሁሉም ቤተ-እምነቶች ጋር በጋራ ችግኝ ተክለናል፤ አረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል ሁላችንም የድርሻችንን ሚና መወጣት አለብን ሲሉም ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሸህ ፈትሁዲን ሀጂ ዘይኑ በበኩላቸው አረንጓዴ አሻራና የኮሪደር ልማቱን ጨምሮ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፍ ሊቸራቸው ይገባል ብለዋል።
ልማቱ ቀጣዩን ትውልድ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን በመገንዘብ ከኛ የሚጠበቀውን ማድረግ ከመንግሥት ጋር ተቀራርቦ መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ተወካይ አባ ጴጥሮስ በርጋ በበኩላቸው አረንጓዴ አሻራ ባህል ሆኖ ቀጣይነት ባለው መልኩ ሊከናወን ይገባል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ እኛ የኃይማኖት አባቶች ትውልዱን ማስገንዘብና ማስተማር ይገባናል ነው ያሉት።
ችግኝ መትከል አንድ እርምጃ ቢሆንም መንከባከብና ለውጤት እንዲበቃ ማድረግ ደግሞ ሌላው ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሃፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ እንዳሉት፤ ጉባኤው በአረንጓዴ አሻራ ላይ የቀረበውን ሀገራዊ ጥሪ ተቀብሎ ችግኝ በመትከል የሚጠበቅበትን ድርሻ እየተወጣ ነው።
ለአብነትም ባለፉት ዓመታት ከ3 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ጉባኤው መትከሉን አስታውሰው በ2016 ዓ.ም ክረምት ወራትም ይህንን ተሳትፎ ለማጠናከር ይሰራል ነው ያሉት።
በአዲስ አበባ ደረጃም የአረንጓዴ ሽፋንን ከፍ ለማድረግ በሚደረገው ርብርብ ጉባኤው የበኩሉን አሻራ ለማሳረፍ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኃይማኖት ተቋማት በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ያላቸውን ሚና እንዲያጠናክሩም ነው የጉባኤው ዋና ጸሃፊ ጥሪ ያቀረቡት።
በአረንጓዴ አራሻ ልማት ዘርፍ የሚያዙ እቅዶች ግባቸውን እንዲመቱ የሁላችንም አስተዋጽኦ ሊታከልበት ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።