የ2016 ዓ.ም የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ከተማ አቀፍ ፈተና ውጤት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/2016(ኢዜአ)፦ የ2016 ዓ.ም የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ከተማ አቀፍ ፈተና ውጤት ይፋ ሆኗል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የአጠቃላይ ካውንስል አባላት በማለፊያ ውጤቱ ዙሪያ ውይይት በማድረግ የማለፊያ ነጥቡን ወስነዋል።


 

በዚሁ መሰረት የ2016 ዓ.ም የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ከተማ አቀፍ ፈተና የማለፊያ ነጥብ 50 ሲሆን ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ደግሞ 45 እንዲሆን የአጠቃላይ ካውንስል አባላት በሙሉ ድምጽ ማጽደቃቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የ2016 ዓ.ም የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ከተማ አቀፍ ፈተና በአጭር ጊዜ ታርሞ ይፋ መደረጉ ተማሪዎች ለቀጣዩ የትምህርት አመት ከወዲሁ በቂ ዝግጅት እንዲያደርጉ የሚያስችል መሆኑም ተጠቅሷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ ውጤቱ ታርሞ ቶሎ እንዲደርስ ቀንና ሌሊት በመስራት ለዚህ ቀን ላደረሱ የፈተና ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ክፍል ባለሙያዎች ምስጋና አቅርበዋል።

በ2016 ዓ.ም የ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ 85 ሺህ 046 በመንግስትና በግል ትምህርት ቤቶች በቀን እና በማታ ትምህርታቸውን ከተከታተሉ ተማሪዎች መካከል 94.3% ያህሉ 50% እና በላይ ማምጣታቸውን በቢሮው የፈተና ዝግጅትና አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ዲናኦል ጫላ መናገራቸውም በመረጃው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም