የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ለትውልዱ የተሻለች ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ መገንባት እንደሚቻል ተምሳሌታዊ ማሳያ ነው - የ12ኛ ክፍል ፈተና አስፈጻሚ መምህራን

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/2016(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ለመጪው ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ መገንባት እንደሚቻል ተምሳሌታዊ ማሳያ ነው ሲሉ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና አስፈጻሚ መምህራንና ሱፐርቫይዘሮች ተናገሩ፡፡

የዘንድሮውን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ሲያስፈፅሙ የቆዩ መምህራንና ሱፐርቫይዘሮች በመዲናዋ የኮሪደር ልማቶችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።


 

የአዲስ አበባን ገፅታ እየቀየረ በሚገኘው የኮሪደር ልማት የመንገድ መሰረተ-ልማት፣ መብራት፣ ፍሳሽ ማስወገጃ ቦዮች፣ የአዳዲስ ቤቶች ግንባታና እድሳት፣ የመዝናኛ ስፍራዎችና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ያካተተ ነው።

የልማት ስራዎቹ በተቀመጠላቸው አቅጣጫና የጊዜ ገደብ እየተከናወኑ ሲሆን አብዛኛዎቹም ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱን የጎበኙ መምህራንና ሱፐርቫይዘሮችም በልማት ስራው መደነቃቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ከጎብኝዎች መካከል የትምህርት ባለሙያው ዓለማየሁ ለማ ከዚህ ቀደም አዲስ አበባ ለስራ ጉዳይ ይመላለሱ እንደነበር አውስተው፥ ለእግረኛ የማይመች መንገድ እና የተጎሳቆለ የከተማ ገፅታን ይመለከቱ እንደነበር አስታውሰዋል።

የኮሪደር ልማቱ በተጀመረ በወራት ጊዜ ውስጥ አዲስ አበባ የገፅታ ለውጥ እንዳሳየችና ውብ እንደሆነች መመልከታቸውንም በአድናቆት ገልጸዋል።

ልማቱ በአጭር ጊዜ በጥራት መከናወኑ እንዳስደነቃቸውና አስተማሪ እንደሆነ ጠቅሰው፥ የከተማዋን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት በከፍተኛ ሁኔታ የሚጨምር መሆኑንም ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቶቹ የተከናወኑበት ፍጥነት እና ጥራት ለሌሎች ከተሞች ምሳሌ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።


 

መምህር ሀሰን አባተ በበኩላቸው፤ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶቹ የላቀ አፈጻጸም በተባበረ ክንድ በአጭር ጊዜ ለውጥ በማመጣት ለትውልዱ የተሻለች ሀገርን ማስረከብ እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል።

በመሆኑም በአዲስ አበባ የተመዘገበው ስኬት በሌሎችም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል።

አዲስ አበባ ለሀገራችን ከተሞች ተምሳሌት ናት ያሉት አቶ ጣዕሙ ኡመለማን፥ ኢትዮጵያ በዕድገትና በለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን የኮሪደር ልማቱ ቋሚ ምስክር ነው ብለዋል።


 

ይህንን መሰል ስራ በትምህርት ዘርፉም ሆነ በሌሎች መስኮች በመተግበር የሀገርን ርዕይ ማሳካት የሁላችንም ሃላፊነት ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም