ቀጥታ፡

መንግስት የጎንደር ከተማን ታሪክና እድገት የሚመጥን ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመፈጸም  በትኩረት እየሰራ ነው- አቶ አህመድ ሽዴ

ጎንደር፤ ሐምሌ 13 ቀን 2016(ኢዜአ)፡- መንግስት የጎንደር ከተማን ታሪክና እድገት የሚመጥን ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ተፈጻሚ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን  የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ በከተማው በተዘጋጀ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ የችግኝ ተከላ በማካሄድ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤  የከተማውን ሕዝብ የዘመናት የልማት ጥያቄና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)  አመራር የተሰጠባቸው የልማት ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲጠናቀቁ በትኩረት ይሰራል፡፡

በአሁኑ ወቅት የመገጭ የመስኖና የመጠጥ ውሃ ግድብ ፕሮጀክት እንዲሁም የአዘዞ ጎንደር የኮንክሪት አስፓልት መንገድ ስራ  በጥሩ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡


 

የጎንደር ከተማን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃትም የፌዴራል መንግስት የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት ዓለም አቀፍ ቅርስ ጥገና ስራን ማስጀመሩንም ገልጸዋል፡፡ 

የከተማውን የኢንቨስትመንት የቱሪዝምና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማሳለጥ ሰላም ወሳኝ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ በዚህ ረገድ የሰላሙ ባለቤት ህዝቡ ራሱ መሆኑን ተገንዝቦ ሰላሙን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ድጋፉን ማጠናከር እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተነሳሽነት የተጀመረው አገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአገራችን ለደን ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ  መቋቋም ፋይዳው የጎላ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ በማሳደግ ለውጤት በማብቃት ረገድ "ተሳትፎውን በማጠናከር እንደ አገር የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት መረባረብ አለበት" ብለዋል፡፡

በክልሉ በአረንጓዴ  አሻራ መርሃ ግብር በርካታ  ችግኞች ተዘጋጅተው በአሁኑ ወቅት የተከላ ስራው በክልሉ የተለያዩ ዞኖችና ከተሞች በመከናወን ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ  በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ  አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ድረስ ሳህሉ ናቸው፡፡


 

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የግብርና ምርታማናት በማሳደግ፣ የተራቆቱ መሬቶችን በደን በማልበስና እንደ አገር የተጀመረውን በምግብ ራስን የመቻል  ንቅናቄ ለማሳካት ምቹ  መደላድል የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ እንደተናገሩት፤  መንግስት ለከተማው ልማትና ኢኮኖሚያዊ እድገት መፋጠን የሰጠው ልዩ ትኩረት በህዝቡና በአመራሩ ዘንድ ትልቅ ደስታን የፈጠረ ነው፡፡


 

የገንዝብ ሚኒስትሩ ወደ ከተማው በመምጣት እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶችን ምልከታ ማድረጋቸው ፕሮጀክቶቹ በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ላይ የፌዴራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደሩ፣ ከፍተኛ አመራር አባላት ፣ የከተማው ነዋሪዎች የ102ኛ ኮር የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ የጦር አዛዦችና አባላት  ተሳትፈዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም