ቀጥታ፡

የክህሎት ልማት ስልጠና በፍላጎት መር አጫጭር  ሥልጠና ላይ ያተኮረ እንዲሆን ዝግጅት ተደርጓል  

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/2016(ኢዜአ)፦ የክህሎት ልማት ስልጠና በፍላጎት መር አጫጭር ሥልጠና ላይ ያተኮረ እንዲሆን ዝግጅት መደረጉን  የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል አስታወቁ፡፡

ሚኒስቴሩ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር በዘርፉ በተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎችና በተገኙ ውጤቶች ላይ ውይይት እያደረገ ይገኛል፡፡

በውይይቱ በትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ፤ በጥቃቅን አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ረቂቅ ፖሊሲ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ምክክር በመደረግ ላይ ነው፡፡

በመድረኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ሎሚ በዶ፣ የሰው ሃብት ልማትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) እና የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚልን ጨምሮ የምክር ቤት አባላትና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡


 

የስራና ክህሎት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በዚሁ ወቅት ተቋሙ ባለፋት አመታት በክህሎት ልማትና የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ለማጠናከር በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ባለፈ በኢንዱስትሪዎች ፍላጎትና በሰለጠነው የሰው ኃይል መካከል ትስስር ለመፍጠር ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

እንደዚሁም በአጫጭር ስልጠና በቂ ክህሎት ያለው የሰለጠነ የሰው ሃይል በማፍራት በውጭ አገር የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ውጤታማ ስራ መሰራቱን ለምክር ቤት አባላት አስረድተዋል ።

በቀጣይ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ያለፉትን አመታት ልምዱን በመቀመር በአዲስ እሳቤ የተለያዩ ተግባራት ለማከናወን ማቀዱን ገልጸዋል።

በዋነኝነት የክህሎት ልማትን  በፍላጎት መር አጫጭር ስልጠና ላይ መሰረት በማድረግ በስፋትና በአዲስ እሳቤ ለመስጠት መታቀዱን አስታውቀዋል።


 

በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን ወደ ተሟላ የዲጂታል አሰራር ለማሸጋገርና በራሳቸው አቅም የሚተዳደሩ ነጻ ተቋማትን ለመገንባት መታቀዱን ይፋ አድርገዋል።

በአሁን ወቅት የዲጂታል አሰራሩን  በ100 ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆች ለመተግበር አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅሰው ከነዚህ ውስጥ 86 ቱ በተለያየ ደረጃ አሰራሩን እየተገበሩ መሆኑን አስረድተዋል።

ፖሊ ቴክኒክኒክ ኮሌጆች በቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሁም በአካባቢዎች የሚገኙ ፀጋዎችን ታሳቢ ያደረጉና በእሴት ሰንሰለት ላይ የተመሠረቱ ስልጠናዎች እንዲሰጡ ትኩረት ይደረጋል ብለዋል።

ይህንን ግብ ለማሳካት በቀጣይ የሰው ሃይል፣ የማሽነሪና የአሰራር አደረጃጀት ለውጥ የሚደረግ መሆኑን አሳውቀዋል።

ይህም ተግባር የተሳካ እንዲሆን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም