ቀጥታ፡

የዘመናት ኤሌክትሪክ ኃይል ጥያቄያችን ምላሽ ማግኘቱ የተሻለ ሕይወት ለመምራት ያስችለናል-የሂግሎሌ ወረዳ ነዋሪዎች

ቆራሄ፤ሐምሌ 13/2016(ኢዜአ)፦የዘመናት የኤሌክትሪክ ኃይል ጥያቄያቸው ምላሽ ማግኘቱ በአኗኗራቸው ላይ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሚያግዛቸው በሶማሌ ክልል ቆራሄ ዞን የሂግሎሌ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በወረዳው በ75 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የፀሐይ ኃይል የኤሌክትሪክ ጣቢያ ትናንት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የገለጹት የወረዳው ነዋሪዎች ጣቢያው በወረዳውና በአካባቢው ለሚገኙ ነዋሪዎችና ተቋማት አገልግሎት መስጠት መጀመሩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄያቸው እንዲመለስ አድርጓል።

ወይዘሮ ሸምሾ አህመድ እንደገለጹት ለዓመታት ሲጠቀሙበት ከነበረው ፋኖስና ላምባ ብርሃን በመገላገላቸው ደስታቸው ወሰን የለውም።

"ዛሬ ከጨለማ ወደ ብርሃን ተሸጋግረናል፤ ኤሌክትሪክ መጠቀም ህይወትን ስለሚያቀል መንግሥትንም እናመሰግናለን " ብለዋል።

ወይዘሮ ሰአዳ ሁሴን የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው በሚኖሩበት የገጠር መንደር ኤሌክትሪክ ተደራሽ መሆኑ "በተለይ ሴቶች በተለያዩ የገቢ ሥራዎች ተሰማርተን ከተረጂነትና ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ለመላቀቅ ያግዘናል" ብለዋል።

በተጨማሪም ሴቶች ማገዶ ፍለጋ የሚያባክኑትን ጊዜና ጉልበት ለልማት እንዲያውሉ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ነው የተናገሩት።

በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ፕሮጀክት ግንባታ ካገኘው የሥራ ዕድል በተጨማሪ በቀጣይ ከሌሎች ወጣቶች ጋር ተደራጅቶ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለመሆን ፕሮጀክቱ እንደሚያግዝ የገለፀው ደግሞ ወጣት አደን ሙመድ ነው።

የኤሌክትሪክ ኃይል መኖሩ ወጣቶችና ሴቶችን በፀጉር ቤት፣ በምግብ ቤት፣ በብረታብረት እና መሰል ሥራዎች ለመሰማራት ዕድል ይፈጥርልናል ብሏል።

ሌላው የወረዳው ነዋሪ አቶ ዳቡድ ወሊ በአካባቢው የኤሌክትሪክ አገልግሎት መጀመሩ ልጆቻቸው ጥራት ያለው ትምህርትና የተሻለ የጤና አገልግሎት ለማግኘት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።

"ዘመኑ የኢንፎርሜሽን ነው፤ በእጃችን የያዝነውን ተንቀሳቃሽ ስልክ ሆነ ሌሎች የኤሌክትሮኒክ ቁሶች ተጠቅመን ኑሯችንን ቀላልና ህይወታችንን የሰመረ ለማድረግ ያስችለናል" ሲሉም አክለዋል።

በወረዳው የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት መጀመሩ የአካባቢውን አርብቶ አደር ኑሮ ለማሳደግና የንግድ እንቅስቃሴ ለማቀላጠፍ ያግዛል ያሉት ደግሞ የማህበረሰብ መሪ ዑጋዝ ፋራህ ሳህል ናቸው።

አገልግሎቱ ዘላቂ እንዲሆን ተገቢውን ጥበቃና እንክብካቤ እናደርጋለን ብለዋል።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ የተመራ የሚኒስቴሩ ከፍተኛ አመራር አባላት በአሁኑ ወቅት በሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን ዳራቶሌ ወረዳ 725 ኪሎዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ የፀሐይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን እየመረቀ ነው።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም