ቀጥታ፡

ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን በኮምቦልቻ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ አንቀሳቃሾች ገለጹ

ደሴ፤ ሐምሌ 13/2016(ኢዜአ)፡-  ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ከመተካት ባለፈ የውጭ ምንዛሪ ለማምጣት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን በኮምቦልቻ ከተማ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ አንቀሳቃሾች ገለጹ፡፡

በኮምቦልቻ ከተማ  በ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ ለፋብሪካዎች በተደረገ ክትትልና ድጋፍ ከ47 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት የተለያየ ተኪ ምርት ማምረት መቻሉን የከተማ አሰተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታውቋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ  በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ከተሰማሩ አንቀሳቃሾች መካከል የኮምቦልቻ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ይገኝበታል።

የፋብሪካው ማርኬቲንግ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሀይደር አራጋው ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ፋብሪካው በዓመት ከአምስት ሚሊዮን ኪሎ ግራም በላይ ክርና ከ14 ሚሊዮን ካሬ ሜትር በላይ ጨርቅ በጥራት እያመረተ ነው። 


 

የተለያዩ ምርቶች በብዛትና በጥራት ተመርተው ከአገር ውስጥ ባለፈ በዓለም ገበያ በማቅረብ የተሻለ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተለይ ምርታማነትን በማሳደግ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ከመተካት ባለፈ የውጭ ምንዛሪ ለማምጣት  የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህም 393 ሺህ 400 ሜትር ስኩየር የተለያየ አንሶላ፣ ፎጣ፣ የተቋማት ዩኒፎርምና ሌሎችንም አልባሳት በማምረት 88 ሚሊዮን ብር የሚገመት ተኪ ምርት ማምረት መቻሉን አብራርተዋል፡፡

እንዲሁም ክር፣ አንሶላና ሌሎች ጨርቃ ጨርቆች ወደ ውጭ በመላክ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት መቻሉን ጠቁመው፤ ለዚህም "የኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቅሰዋል፡፡

''በኢትዮጵያ ታምርት'' ንቅናቄ ምርታማነትን በጥራትና በብዛት በማሳደግ ተወዳዳሪ ለመሆን ምቹ ሁኔታ የፈጠረላቸው መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የራስ ጉባ ዱቄትና ብስኩት ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል አበራ ናቸው፡፡


 

ከውጭ የሚመጣውን የስንዴ ዱቄት በአገር ውስጥ ለመተካት በተደረገ ጥረት አበረታች ውጤት መመዝገቡንም ገልጸዋል፡፡

ፋብሪካው ብስኩትና ዱቄት ከማምረት ባለፈ ማሾ፣ ቀይና ነጭ ቦለቄ፣ አኩሪ አተርና የቅባት እህሎች ላይ እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፋብሪካው የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ የተሻለ የሰው ኃይል እንዲፈጠርም አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቁመው፤ ከ400 ለሚበልጡ ሰዎችም  የሥራ ዕድል መፈጠር መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በኮምቦልቻ ከተማ  አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ የኢንዱስትሪ ልማት ቡድን ተወካይ አቶ መሃመድ አደም፤  በከተማው የሚንቀሳቀሱ ፋብሪካዎች ምርታማነታቸውን በጥራት በማሳደግ ተኪ ምርት እንዲያመርቱ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡


 

በዚህም የተሸከርካሪ፣ የወፍጮና የፋብሪካ ማሽን መለዋወጫ ቁሳቁሶችን፣ የተለያዩ አልባሳትና የኢንዱስትሪ ምርቶች እንዲመረቱ በማድረግ በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት አበረታች ስራ መከናወኑን ተናግረዋል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ''በኢትዮጵያ ታምርት'' ንቅናቄ በተደረገ ድጋፍ "በ20 ፋብሪካዎች ከ20 ሺህ 600 ቶን በላይ የተለያየ ምርት ተመርቶ ከውጭ የሚመጣ ምርት በአገር ውስጥ ምርት መተካት ተችሏል" ብለዋል፡፡

በተደራጀ አግባብ በተደረገ ድጋፍም ሰባት ፋብሪካዎችም አጋጥሟቸው የነበረው ችግር በመፍታት ወደ ማምረት እንዲገቡ ማድረግ መቻሉን አስረድተዋል።

ተኪ ምርት ከማምረት ባለፈም በሰባት ፋብሪካዎች ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ከ48 ሺህ 800 ቶን በላይ የቅባት፣ የአልባሳትና ሌሎችም ምርቶች  መመረታቸውን ገልጸዋል።

ፋብሪካዎች ተኪ ምርት ከማምረትና የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘት በተጨማሪም የቴክኖሎጅ ሽግግርና የስራ እድል ለመፍጠር ምቹ መሆናቸውን አቶ መሃመድ አመልክተዋል፡፡

በኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 45 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 148 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም