ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በመቀሌ ከተማ ዙሪያ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ - ኢዜአ አማርኛ
ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በመቀሌ ከተማ ዙሪያ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኖሩ
መቀሌ ፤ ሐምሌ 13/2016(ኢዜአ)፦ ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በመቀሌ ከተማ ዙሪያ ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
"በጎነትና አብሮት ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሐሳብ የተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተዘጋጀው ነው።
ይህም ወሰን ተሻጋሪ ወጣቶች በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች የሚያከናውኑት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር አካል መሆኑም ተመላክቷል።
ወጣቶቹ ከሰኔ 27 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ክልሎች በመዘዋወር ችግኝ በመትከል፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ እና አረጋውያንን በመርዳት በጎ ተግባር እየፈጸሙ ነው።
በተጨማሪም የደም ልገሳ፣ የጽዳትና መሰል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎችን ማከናወናቸውን በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ አስተባባሪ አቶ እንደገና ፍቃዱ ገልፀዋል።
የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፈቃድ አገልግሎት ወጣቱ በአረንጓዴ አሻራ እና በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሳተፍ አሻራውን ከማኖር ባለፈ አብሮነትና አንድነትን የማጠናከር ዓላማ እንዳለው አስረድተዋል።
በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ በበኩላቸው፤ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ተዘዋውረው በበጎ ተግባር መሳተፋቸው ደስታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
የየአካባቢውን ባህል፣ ልምድ እና ወግ በቅርበት ለማወቅና የእርስ በርስ ግንኙነትን ለማጠናከር እንዳገዛቸውም ገልጸዋል።