የሰው ሰራሽ አስተውሎት የታዳጊዎች የክረምት መርሀ ግብር ስልጠና ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የሰው ሰራሽ አስተውሎት የታዳጊዎች የክረምት መርሀ ግብር ስልጠና ተጀመረ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/2016(ኢዜአ)፦ ሶስተኛው ዙር የሰው ሰራሽ አስተውሎት የታዳጊዎች የክረምት መርሀ ግብር ስልጠና ተጀመረ።
የሰው ሰራሽ አስተውሎት የታዳጊዎች የክረምት መርሀ ግብር ስልጠና ችግር ፈቺ ምርምር በማድረግ በዘርፉ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማጎልበት የሚያስችል መሆኑን የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ገለጿል።
የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሶስተኛው ዙር የታዳጊዎች የክረምት ስልጠና ማስጀመሪያ መርኃ ግብር በሳይንስ ሙዚየም ተከናውኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገትና የኢኮኖሚ ሽግግር አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የማይተካ ሚና እንዳለው በመግለጽ በዘርፉ ላይ መስራት እንደሚገባ በተለያዩ መድረኮች ማንሳታቸው ይታወሳል።
በተለይም ትውልዱ ላይ መልካም ዘር በመዝራት የወደፊቷን የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ እንደሚገባም ማሳሰባቸው እንዲሁ።
ኢትዮጵያ ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ተነጥላ መቀመጥ እንደማትችልና በዘርፉ እየተከናወነ ያለው ስራ አበረታች መሆኑንም መጠቆማቸው አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ ለሶስተኛው የታዳጊዎች የክረምት ስልጠና መርኃ ግብር ከሶስት ሺህ በላይ ታዳጊዎች ተመዝግበው 201 ተመርጠዋል።
በዓለም ላይ በፍጥነት እያደገ የመጣውን የሰው ሰራሽ አስተውሎት የሚመጥን የሰው ሀይል ለማፍራት በታዳጊዎች ላይ መስራት ይገባል ብለዋል።
ለዚህም በሰው ሰራሽ አስተውሎት ምርምር በማድረግ የሀገራቸውን ችግር የሚፈቱና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን መስራት የሚችሉ ታዳጊዎችን እያሰለጠኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት የክረምት ሰልጣኝ ታዳጊዎች ችግር ፈቺ ፕሮጀክቶችን እንዲያፈልቁ ለማስቻል አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።