በስፔን ማድሪድ ብሄራዊ ቤተ-መጻሕፍት የኢትዮጵያ ቤተ-መጻሕፍት ክፍል ተከፈተ - ኢዜአ አማርኛ
በስፔን ማድሪድ ብሄራዊ ቤተ-መጻሕፍት የኢትዮጵያ ቤተ-መጻሕፍት ክፍል ተከፈተ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/2016(ኢዜአ)፦በስፔን ማድሪድ ብሄራዊ ቤተ-መጻሕፍት የኢትዮጵያ ቤተ-መጻሕፍት ክፍል ተከፈቷል።
በሃገሪቱ ብሄራዊ ቤተ-መጻሕፍት ቅጥር ግቢ የተደራጀው ይኸው የኢትዮጵያ ቤተ-መጻሕፍት ክፍል የኢትዮጵያን ታሪክ ባህልና ቋንቋ ለተቀረው አለም ለማስተዋወቅ እንዲረዳ መደራጀቱን የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ውብአየሁ ማሞ ገልፀዋል።
መጻሕፍቶቹን በስፔን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሚገባ እንዲጠቀሙባቸው አመች በሆነ የዲጂታል መተግበሪያዎች ሳይቀር መገኘት እንደሚችሉ ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት።
ኢትዮጵያና ስፔን ያላቸውን መልካም ግንኙነት መሰረት በማድረግ በሃገሪቱ ብሄራዊ ቤተ-መጻሕፍት የተደራጀው የኢትዮጵያ መጻሕፍት ክፍል የሁለቱ ሃገራት የቆየ ወዳጅነት ይበልጥ እንዲጠናከር እንደሚያግዝም ኢንጂነር ውብአየሁ ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም የአብርሆት ቤተ መጻሃፍት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፣የአውሮፓ ህብረት እና ትብብር ተጠሪ ጉሌርሞ ኢስክቫኖ ጋር በመተባበር ኢትዮጵያውያን የስፓኒሽ ቋንቋ በነፃ እንዲማሩ መግባባት ላይ ስለመደረሱም አውስተዋል።
የስፔን ብሄራዊ ቤተ መጻሕፍት ከ26 ሚሊዮን በላይ የመጻሕፍት ስብስቦችን በመያዝ በአለማችን ላይ ከሚገኙ ስመጥር ቤተ-መጻሕፍት ተርታ የሚሰለፍና ታሪካዊ ሲሆን የተመሰረተውም እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን አቆጣጠር በ1711 መሆኑ ተገልጿል።
ቤተ-መጻሕፍቱ በኦንላይን የሚገኙ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዲጂታል መጻሕፍትንም ያካተተ ሲሆን ለተማሪዎች ለተመራማሪዎችና ለአጠቃላይ አንባቢያን ምቹ የሆኑና በአንድ ጊዜ በርካታ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችሉ የጥናት ክፍሎችም አሉት።