ለአራት አመታት ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ውጪ የነበሩ አካባቢዎች ወደ አገልግሎት ተመለሱ - ኢዜአ አማርኛ
ለአራት አመታት ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ውጪ የነበሩ አካባቢዎች ወደ አገልግሎት ተመለሱ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/2016(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል አራቱም የወላጋ ዞኖች ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ ችግር የወደሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ በተሰራው የመልሶ ጥገና ስራ ለአራት አመታት ከኤሌክትሪክ አገልሎት ውጪ የነበሩ ከተሞችና መንደሮች ዳግም የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
በቄለም ወለጋ ዞን ዳሌ ሰዲ ወረዳ የሚገኙ ሳጠኖ ዲማና ቤለም አካባቢዎች ከ4 ዓመታት በኋላ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘታቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል፡፡
በዳሌ ሰዲ ወረዳ የሚገኙ ደንበል ሱልጣን እና ሐረሬ ኦግኦ የሚባሉ ቦታዎችም ከ2 ዓመታት በኋላ ተቋርጦ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ዳግም እንዲያገኙ ተደርጓል ብሏል፡፡
በሌላ በኩል ምስራቅ ወለጋ ዞን ግዳ አያና ወረዳ አንገር ጉትን ከተማ በርካታ መንደሮች እና ለሊ ቀበሌ እንዲሁም ገባ ፈጫሴ፣ ጠንከራና ቦነያ ጤና ጣቢያ የሚባሉ ስፍራዎች ከ2 እስከ 4 ዓመታት በኋላ ዳግም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልጿል፡፡
በተያያዘም በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አባቦ ጉዱሩ ወረዳ ገባ ፈጫሴ፣ ቃዎ፣ ሀለዮ፣ ቆርቾ እና ገባ ፈጫሴ ቴሌኮም ተብለው የሚጠሩ ቦታዎች ከ2 እስከ 3 ዓመታት ቆይታ በኋላ አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጋቸውንም አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም በምዕራብ ወለጋ ዞን ዩብዶ ወረዳ መለያ ዩብዶ ቀበሌ ከአንድ ዓመት በኋላ አገልግሎት ማግኘቷን ተጠቁሟል፡፡
እነዚህን 18 ቀበሌዎችና ከተሞችን ዳግም ከኤሌክትሪክ ጋር ለማገናኘት በተሰራው ስራ ከ78 ኪ.ሜ በላይ ዳግም የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታና ጥገና እንዲሁም 19 ትራንስፎርመሮችን መተካቱንም አመላክቷል፡፡
በወላጋ ዞኖች በጸጥታ ችግር ምክንያት የወደሙና የተጎዱ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን መልሶ የመጠገን ስራ የቀጠለ ሲሆን በእስካሁኑ ስራ በዞኖቹ ከ85 በላይ ከተሞችና ቀበሌዎች ዳግም ኤሌክትሪክ ማግኘታቸው ተገልጿል፡፡