የተሻሻለው የኢትዮጵያ የጤና ፖሊሲ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተያዙ ዘላቂ የጤና ግቦችን ለማሳካት ይረዳል - ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ - ኢዜአ አማርኛ
የተሻሻለው የኢትዮጵያ የጤና ፖሊሲ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተያዙ ዘላቂ የጤና ግቦችን ለማሳካት ይረዳል - ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13/2016(ኢዜአ)፦ የተሻሻለው የኢትዮጵያ የጤና ፖሊሲ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተያዙ ዘላቂ የጤና ግቦችን ለማሳካት ይረዳል ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ገለጹ።
ሚኒስትር ዴኤታው በቻይና ቤጂንግ በተካሄደው 3ኛው የዓለም የጤና ፎረም ላይ ተሳትፈዋል።
በፎረሙ ላይም ዶክተር ደረጄ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ለጤናው ዘርፍ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን አንስተው፤ ለዘርፉ በምታደርገው ጥረት ወሳኝ ወቅት ላይ እንዳለች ገልጸዋል።
እንደ አፍሪካ አህጉርም ጠንካራ፣ ፍትሃዊ እና ዘላቂ የጤና ስርዓቶችን በመፍጠር ረገድ ያሉ ዕድሎችንና ተግዳሮቶችን አብራርተዋል።
ሁሉን አቀፍ ጤናን ለማረጋገጥ በኢትዮጵያ አዲስ የጤና ፖሊሲ ተቀርጾ ወደ ስራ መገባቱን የጠቆሙት ዶክተር ደረጀ፤ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተያዙ ዘላቂ የጤና ግቦችን በኢትዮጵያ ለማሳካት ይረዳል ብለዋል።
ፖሊሲው ለዜጎች የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶችን ለማሻሻል እንዲሁም ፍትሃዊና ለሁሉ ተደራሽ የጤና ስርዓት ለማስፈን እንደሚረዳም ጠቁመዋል።
አፍሪካውያን የአህጉራቸውን የጤና ሁኔታ በላቀ ደረጃ ለማሻሻል በትብብር መስራት እንዳለባቸው መጠቆማቸውን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።