ቀጥታ፡

በምዕራብ ጎንደር ዞን ህብረተሰቡን በማሳተፍ የወባ በሽታን የመከላከል ተግባር በመከናወን ላይ ይገኛል

መተማ፤ ሐምሌ 13/2016(ኢዜአ)፦ በምዕራብ ጎንደር ዞን የወባ በሽታን ለመከላከል ህብረተሰቡን በማሳተፍ የአካባቢ ቁጥጥር ስራ እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ።

በመምሪያው የወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያ አቶ አህመድ አሊ፤ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ለወባ በሽታ ተጋላጭ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአካባቢው ከሚከናወን ሰፊ የግብርና ስራ ጋር ተያይዞ ከነዋሪዎች በተጨማሪ የጉልበት ሰራተኞች በስፋት የሚሰማሩበት በመሆኑ የወባ በሽታ ለመከላከል ጠንካራ የተቀናጀ ስራ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።


 

ለዚህም ከወዲሁ ህብረተሰቡን በማሳተፍ የወባ ትንኝ መራቢያ ሥፍራዎችን የማፋሰስና ረግረጋማ ቦታዎችን የማዳፈን ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በተለይም ቀደም ሲል ችግሩ ጎልቶ ይታይበት በነበረው አዳኝ አገር ጫቆ ወረዳ የኬሚካል ርጭት መካሄዱን ጠቅሰው፤ በሌሎች ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ህዝቡን ያሳተፈ ንቅናቄ እየተተገበረ ነው ብለዋል።

በዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ የሚመራ ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ እስከ ቀበሌ ድረስ በሽታውን ለመከላከል የተከናወኑ ስራዎችን እንደሚከታተል የተናገሩት ባለሙያው "ወባን ለማጥፋት ከእኔ ይጀምራል" በሚል መሪ ሀሳብ ዘመቻ በተያዘው ወር መጀመሩን ጠቁመዋል።


 

አስቀድሞ ከመከላከል በተጨማሪ በቂ የህክምና ቁሳቁስ እንዲሟላ መደረጉንም አብራርተዋል።

ከሰኔ ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ በተደረገው የደም ምርምራ በበሽታው ተይዘው ለተገኙ ሰዎች ተገቢው የህክምና አገልግሎት መሰጠቱን አብራርተዋል።

የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪ አቶ መሰለ ስመኘው በሰጡት አስተያየት፤ ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ የሆኑና ውሃ የሚቋጥሩ ጉድጓዶችን የማዳፈንና የማፅዳት ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አጎበር በአግባቡ እንደሚጠቀሙም አቶ መሰለ ጨምረው ተናግረዋል።

ወጣት ቶማስ አበራ በበኩሉ፤ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ በመሳተፍ የወባና ሌሎች ውሃ ወለድ በሽታዎችን ለመከላከል እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም