ቀጥታ፡

በአምስት ዓመታት ከ300 በላይ መካከለኛ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ይገነባሉ

ቆራሄ፤ ሐምሌ 12/2016 ዓ.ም (ኢዜአ)፦በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከ300 በላይ መካከለኛ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን በመገንባት የአገሪቱን የገጠር ቀበሌዎች ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) ገለጹ። 

በሶማሌ ክልል በ75 ሚሊዮን ብር የተገነባው የሂግሎሌ ወረዳ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ተመርቆ ዛሬ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

ፕሮጀክቱን መርቀው ሥራ ያስጀመሩት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ ናቸው።

ሚኒስትር ዴኤታው በዚህ ወቅት እንደገለጹት የተመረቀው ጣቢያ ከ5 ሺህ 600 በላይ ቤተሰቦችን ጨምሮ በሂግሎሌ ወረዳ የሚገኙ ጤና ተቋማት እና ትምህርት ቤቶችን ተጠቃሚ ያደርጋል።


 

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከዋና የኤሌክትሪክ ማሰራጫ አካባቢዎች በራቁ ገጠራማ አካባቢዎች የተገነቡ የፀሐይ ሐይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች  አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንም አስታውሰዋል።

መንግስት ከፀሐይ የሚገኝ የተፈጥሮ ኃይልን በስፋት በሥራ ላይ ለማዋል ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

"ለእዚህም 57 ሚሊዮን ህዝባችንን አማራጭ ቴክኖሎጂ እና የፀሐይ ኃይልን በመጠቀም ወደ ብርሃን ለማሻገር በትኩረት እየሰራን እንገኛለን" ብለዋል።

በሚቀጥሉት 5 ዓመታት ብቻ ከዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶችና ባለድርሻዎች ጋር በመሆን ከ300 በላይ መለስተኛ የፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ ማመንጫ ጣቢያዎች በአርብቶና አርሶ አደሩ ቀበሌዎች ይገነባሉ ሲሉም ገልጸዋል።

በምረቃው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ በበኩላቸው፣ ተቋማቸው ዋና ዋና የኤሌክትሪክ መስመሮችን እንደሚያስፋፉ ገልጸዋል።


 

ከእዚህ ጎን ለጎን ከዋና የኤሌክትሪክ መረብ ርቀው የሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች እና መንደሮችን የፀሐይ ኃይል ማመንጫ በመገንባት ፍትሃዊ የኤሌክትሪክ ሃይል ተደራሽነት እንዲረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ነው ያስረዱት። 

"ዘንድሮ ተደራሽ ከሆነባቸው 116 ከተሞች ውስጥም 8ቱ በሶማሌ ክልል የሚገኙ ናቸው" ብለዋል።

ለምጣኔ ሃብት እና ለማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ስኬት የኤሌክትሪክ ሃይል አስተዋጾ የጎላ ነው ያሉት ደግሞ በሶማሌ ክልል የቆራሄ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሻፊ መሐመድ ናቸው።

እሳቸው እንዳሉት ዛሬ ተመርቆ በገጠር እና በወረዳ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የፀሐይ ኃይል የአርብቶ አደሩን ህይወትና አኗኗርን በከፍተኛ ደረጃ ይለውጣል።

"የአርብቶ አደር ልጆች እና ማህበረሰቡ የተሻለ ትምህርትና የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል፤ የብልፅግና ጉዞ ፍሬያማነትም በተግባር እየተረጋገጠ ይመጣል" ብለዋል።

ዛሬ በቆራሄ ዞን ሂግሎሌ ወረዳና ገጠር ከተማ በተካሄደ የምረቃ ሥነስርዓት ላይ የፌደራል እና የሶማሌ ክልል ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ዑጋዞች እና በየደረጃው ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም