የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብታዊ ዕምርታን ዘላቂነት ለማረጋገጥ ምሁራን የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል- ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብታዊ ዕምርታን ዘላቂነት ለማረጋገጥ ምሁራን የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል- ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብታዊ ዕምርታን ዘላቂነት ለማረጋገጥ ምሁራን በችግር ፈች ጥናትና ምርምር እንዲደግፉ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ጥሪ አቀረቡ።
ፕሮፌሰሩ ይህን ያሉት የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ማህበር ዛሬ ባካሄደው 21ኛው ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
በጉባዔው በማምረቻው፣ በፋይናንስ፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በግብርና እና በሌሎች ዘርፎችና የማክሮ ኢኮኖሚ ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች ላይ በቀረቡ ጥናታዊ ፅሁፎች ላይ ውይይት ተደርጓል።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ እንዳሉት፤ በትግበራ ላይ የሚገኘው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ስኬት የምሁራን ተሳትፎ ይሻል።
በኢትዮጵያ እየተመዘገበ ያለው ምጣኔ ሃብታዊ እምርታ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ያነሱት ፕሮፌሰሩ፤ የእድገቱን ዘላቂነት ለማረጋገጥ የምሁራንና የሙያ ማህበራት ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል።
በተለይም ዘላቂ የልማት ዕቅዶችን በመተግበር የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ እና ዘላቂ ሀገራዊ ዕድገት ለማስቀጠል የምጣኔ ሀብት ምሁራን በሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር መደገፍ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
በዚህ ረገድ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ማህበርን ጨምሮ ከተለያዩ የሙያ ማኅበራት ጋር በትብብር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ማኅበር ዋና ስራ አስፈጻሚ ፕሮፌሰር መንግስቱ ከተማ በበኩላቸው፤ ማህበሩ በሀገራዊ የምጣኔ ሃብት ፖሊሲዎችና መርሃ ግብሮች የሚበጁ ምክረ ሃሳቦችን ሲያቀርብ ቆይቷል።
ለአብነትም በትግበራ ላይ በሚገኘው የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድን ጨምሮ በሀገራዊ የልማት ዕቅዶች ዙሪያ ጥናቶችን በማካሄድ ሳይንሳዊ ምክረ ሃሳቦችን ለመንግስት ማቅረቡን አስታውሰዋል።
በቀጣይም የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብታዊ ዕምርታን ዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚበጁ በጥናትና ምርምር ላይ የተመሰረቱ ምክረ ሃሳቦችን የማቅረብ ልምዱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በጉባኤው በማክሮ ኢኮኖሚ፣ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ፣ በፋይናንስ ዘርፍ፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በግብርና እና ሌሎች የምጣኔ ሃብት ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበዋል።
በማኅበሩ የምርምርና ፖሊሲ ትንተና ዳሬክተር ደግዬ ጎሹ (ዶ/ር) በማክሮ ኢኮኖሚ ዕድሎችና ፈተናዎች ላይ ባቀረቡት ፅሁፍ የሀገራዊ ምርትና ምርታማነት አቅምን ለመጠቀም ሰላምና ጸጥታ ያለውን ወሳኝ ሚና ጠቁመዋል።
በማህበሩ ከፍተኛ ተመራማሪው ለሜሳ ታሪኩ (ዶ/ር) በማምቻው ዘርፍ ዕድሎችና ፈተናዎች ዙሪያ ባቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፍ እንደጠቆሙት፤ ዘርፉ ባለፉት 3 ዓመታት በውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ክፉኛ ተፈትኗል።
የማምረቻው ዘርፍ ለኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ገቢ ተጠቃሽ ከሚባሉ ዘርፎች ውስጥ የሚጠቀስ በመሆኑ በቀጣይ የምርት ስብጥርና የገበያ መዳረሻ በትኩረት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ መክረዋል።
ነገ በሚቀጥለው 21ኛው ዓለም አቀፍ ጉባኤ በድህነት ቅነሳ፣ አየር ንብረት ለውጥ፣ በዋጋ ንረትና ሌሎች ጉዳዮች ላይ በተደረጉ ጥናቶች ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።
በየዓመቱ ሀምሌ ወር የሚደረገው ይህ ዓለም አቀፍ ጉባዔ ማህበሩን ጨምሮ የምርምር ተቋማት ጥናታዊና የምርምር ውጤቶች ለውይይት ቀርበው ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ምክረ ሃሳብ የሚወጡበት መድረክ ነው።