የትኛውም ፀረ ሰላም ኃይል በመዲናዋ ለመፈጸም የሚያስበውን የሽብር ተግባር ማክሸፍ የሚያስችል ጠንካራ ፖሊስ ኅይል ተገንብቷል-ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው - ኢዜአ አማርኛ
የትኛውም ፀረ ሰላም ኃይል በመዲናዋ ለመፈጸም የሚያስበውን የሽብር ተግባር ማክሸፍ የሚያስችል ጠንካራ ፖሊስ ኅይል ተገንብቷል-ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2016(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ የትኛውም ፀረ ሰላም ኃይል የሚያስበውን የሽብር ተግባር ማክሸፍ የሚያስችል በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና በሎጂስቲክስ አቅሙ የተጠናከረ ፖሊስ ኅይል ተገንብቷል ሲሉ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ተናገሩ።
ፖሊስ በበጀት ዓመቱ በቅንጅት ባከናወናቸው ጠንካራ የወንጀል መከላከል ስራዎች በህዝብ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድሩ ከባድ ወንጀሎችን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ መቻሉን አረጋግጠዋል።
ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በ2016 በጀት ዓመት ያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ ዛሬ ለመገናኛ ብዙኅን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚህም የአዲስ አበባ ፖሊስ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ መዲና የሆነችውን የአዲስ አበባን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ ቀዳሚ ኃላፊነት ይዞ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
የወንጀል መከላከል፣ ሰላምና ደኅንነትን የማስጠበቅ ተቋማዊ አቅምን ማጎልበት የሚያስችል ስኬታማ የለውጥ እርምጃ መወሰዱንም ተናግረዋል።
በለውጥ እርምጃዎቹም የጸረ-ሰላም ኃይሎችን ሴራ በማክሸፍ እንዲሁም ኃማኖታዊና ህዝባዊ የአደባባይ በዓላትንና ስፖርታዊ ክዋኔዎችን በሰላማዊ መንገድ ማካሄድ እንደተቻለ አንስተዋል።
የመዲናዋን ሰላምና ደኅንነት ለማደፍረስ ሲንቀሳቀሱ በተገኙ ጸረ-ሰላም ኃይሎች ላይ በተወሰደው እርምጃም በሀገር ላይ ሊደርስ የነበረን ከፍተኛ አደጋ መቀልበስ የተቻለበት ስኬታማ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።
በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ሚሊኒዬም አዳራሽ አካባቢ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቃሰቀሱ የነበሩ 38 የፅንፈኛው ቡድን አባላትን ከጸጥታ አካላት ጋር በመተባበር በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ ባልሆኑ የቡድኑ አባላት ላይ እርምጃ መወሰዱን አስታውሰው፣ የሽብር ቡድኑ በህዝብ ላይ ሊያደርስ የነበረውን ጥፋት ማክሸፍ መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በወንጀል መከላከል ረገድ በማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት በስርቆትና ተያያዥ ከቀላል እስከ ከባድ የወንጀል ድርጊት የፈጸሙ አካላትን በቁጥጥር ስር በማዋል በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጉን አስረድተዋል።
ጥናትን መሰረት በማድረግ በተሰሩ ስኬታማ የኦፕሬሽን ስራዎች በቡድን ተደራጅተው በዜጎች ህይወትና ንብረት ላይ ወንጀል የፈጸሙ አካላትን በቁጥጥር ስር በማዋል ከ13 ሺህ በላይ መዛግብት ተደራጅተው ለዓቃቢ ሕግ መላካቸውን አንስተዋል።
በዚህም የተዘረፉ ተሽከርካሪዎች፣ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችንና የመኪና መለዋወጫዎችን ጨምሮ በርካታ የንብረት አይነቶችን ማስመለስ እንደተቻለ ገልጸዋል።
አደንዛዥ ዕፆችን ሲጠቀሙና ሲያስጠቅሙ እንዲሁም ቁማር ሲያጫውቱ የተገኙ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ተደርጓል ብለዋል።
በበጀት ዓመቱ የተለያየ አይነት የጦር መሳሪያና ተተኳሾችን፣ የመገናኛ ራዲዮ፣ ሕገ-ወጥና ሀሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን ጨምሮ በርካታ የአገር ውስጥና የሌሎች ሀገራት ገንዘብ ኖቶች መያዛቸውን አስረድተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ የመዲና አካባቢዎች በህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ልዩ ልዩ ኤግዚቢቶች መያዛቸውንም አስታውቀዋል።
በበጀት ዓመቱ በተወሰዱ ፖሊሳዊ እርምጃዎች 7 ሺህ 405 ከባድ እና ከ26 ሺ በላይ መካከለኛ ወንጀል የፈጸሙ አካላት እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ገልጸዋል።
ፖሊስ በበጀት ዓመቱ በነበረው ጠንካራ የወንጀል መከላከል ስራም የህዝብ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድሩ ከባድ ወንጀልን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ መቻሉን አስረድተዋል።
ለዚህ ደግሞ የሕዝብ ተሳትፎ ማደጉ፣ የፀጥታ አካላት ቅንጅታዊ አሰራሮች መጠናከራቸው፣ የወንጀል መንስኤዎችን በማጥናት ጥብቅ ቁጥጥር መደረጉና በበቂ ጥናት ላይ የተመሰረቱ ኦፕሬሽኖች ትልቅ ሚና ነበራቸው ነው ያሉት።
በዚህ ሂደት የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደጎን በመተው የዲሲፕሊን ጥሰት የፈጸሙ በርካታ የፖሊስ አመራሮችና አባላት ላይ ከቀላል እስከ ከባድ እርምጃ እንደተወሰደባቸውም ጠቅሰዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ የትኛውም ፀረ ሰላም ኃይል የሚያስበውን የሽብር ተግባር ማክሸፍ የሚያስችል በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና በሎጂስቲክስ አቅሙ የተጠናከረ ፖሊስ መገንባቱም ገልጸዋል።
በቀጣይም ፖሊስ በተደራጀ መንገድ የሚፈፀሙ ወንጀሎች እና የሽብር ተግባራትን የመከላከልና የማክሸፍ ተልዕኮውን ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በመዲናዋ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት እና ሌሎች የልማት ስራዎች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ እና የተለያዩ የወንጀል ተግባራት የሚፈጽሙ አካላት ላይ ቁጥጥር እንዲደረግ መመሪያ መሰጠቱንም ተናግረዋል።