የተ.መ.ድ 4ኛው የፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ በቀጣይ ሣምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
የተ.መ.ድ 4ኛው የፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ በቀጣይ ሣምንት በአዲስ አበባ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2016(ኢዜአ)፦የተ.መ.ድ 4ኛው የፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ ከመጪው ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፤ ቅድመ ጉባኤውን ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ ከተ.መ.ድ ጋር በተደረገ ውይይት መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል።
ቅድመ ጉባኤው፤ በስፔን ከሚካሄደው 4ኛው የፋይናንስ ለልማት ዋና ጉባኤ አስቀድሞ የሚካሄድ መሆኑን ጠቅሰው የስብሰባው ዋነኛ ዓላማ በተ.መ.ድ 2030 ዘላቂ የልማት ግቦች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚመክር ተናግረዋል።
በጉባኤው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የአባል አገራት የፋይናንስ ሚኒስትሮች እንዲሁም የበርካታ ዓለም አቀፍ የዘርፉ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች እንደሚገኙ አመላክተዋል።
በጉባኤው የተ.መ.ድ 2030 ዘላቂ የልማት ግቦች አፈጻጸሙ ያለበት ደረጃ ያጋጠሙ ክፍተቶች እንደሚገመግሙና ቀጣይ እርምጃዎች የሚለዩበትና የመፍትሔ ኃሳቦችን የሚመላከቱበት መሆኑንም ነው ያስረዱት።
ጉባኤው በአዲስ አበባ መካሄዱ ኢትዮጵያ ያላትን የባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ሚና ለማስቀጠል እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።
ከ1000 በላይ እንግዶች በጉባኤው እንደሚሳተፉ የገለጹት ቃል አቀባዩ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት ለጉባኤው መሳካት አስፈላጊውን ዝግጅት መጠናቀቃቸውን አንስተዋል።
የጉባኤው ተሳታፊዎች በተለመደው ኢትዮጵያዊ የእንግዳ አቀባበል እንደሚስተናግዱም አረጋግጠዋል።