የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአርብቶ አደሩ አካባቢዎች የመስኖ ልማት ለማስፋፋት ትኩረት መሰጠቱን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአርብቶ አደሩ አካባቢዎች የመስኖ ልማት ለማስፋፋት ትኩረት መሰጠቱን ገለጸ
ጂንካ፣ሐምሌ 12/2016 (ኢዜአ)፡-የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአርብቶ አደሩ አካባቢዎች እየተካሄደ ያለውን የመስኖ ልማት ለማስፋፋት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ ገለጸ።
ቢሮው በደቡብ ኦሞ ዞን ኛንጋቶም ወረዳ የመስኖ ተቋማትን ለማጠናከር ከ4 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ሁለት ትራንስፎርመሮችን ድጋፍ አድርጓል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ሀብቴ ለኢዜአ እንደተናገሩት የአርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና ከተረጂነት ለማውጣት በክልሉ አርብቶ አደር አካባቢዎች ከ17 በላይ የመስኖ ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ተቋማቱ በነዳጅ የሚሰሩ የውሀ መሳቢያ ሞተር ፓምፖች የሚጠቀሙ በመሆናቸው የማልማት አቅማቸው ውስን ሆኖ መቆየቱን ኃላፊው ተናግረዋል።
ቢሮው ችግሩን ለመፍታት በመስኖ ተቋማቱ በነዳጅ የሚሰሩትን የውሃ መሳቢያ ሞተር ፓምፖች በኤሌክትሪክና በፀሐይ ኃይል በሚሰሩ ሞተሮች ለመተካት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚሁ ሲባል በወረዳው በልማቱ ለተሰማሩ ለአይፓና ለናፒቶኮይት የመስኖ ተቋማት የሚገለገሉባቸው ትራንስፎርመሮች ድጋፍ መደረጉን አመልክተዋል።
ትራንስፎርመሮቹ የመስኖ ተቋማቱን የኃይል አቅርቦት ችግር በመቅረፍ የአካባቢው አርብቶ አደሮች በስፋት በመስኖ ልማቱ በመሳተፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያግዛሉ ብለዋል።
ትራንስፎርመሮቹ እያንዳንዳቸው 315 ኪሎ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያላቸው መሆናቸውንም አቶ ታረቀኝ ገልጸዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የኛንጋቶም ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም ቦንጎዞ፣ የአካባቢው አርብቶ አደሮች በመስኖ ልማቱ ለመሳተፍ የሚያሳዩት ተነሳሽነት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
በወረዳው አገልግሎት የሚሰጡ የመስኖ ተቋማት በነዳጅ የሚሰሩ በመሆናቸው ልማቱን በስፋት ለማከናወን እንዳልተቻለ አመልክተው፣ ለልማቱ የሚያስፈልገው ነዳጅ ፍጆታ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።
በወረዳው የመስኖ ተቋማቱ የኃይል አማራጭ ወደ ኤሌክትሪክ ሲቀየር የሚለማውን መሬት መጠን በእጥፍ ለማሳደግ ያስችላል ብለዋል።
ቢሮው ከዚህ ቀደም ለወረዳው የእርሻ ትራክተር ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፣የአርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለውን ድጋፍ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።