በሂግሎሌ ወረዳ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በሂግሎሌ ወረዳ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ
ሂግሎሌ፤ ሐምሌ 12/2016(ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል ሂግሎሌ ወረዳ 600 ኪሎ ዋት የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ሚኒ-ግሪድ ፕሮጀክት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።
ፕሮጀክቱን መርቀው ዛሬ አገልግሎት ያስጀመሩት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ እና የሶማሌ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ናቸው።
በሥነስርዓቱ ላይ የተገኙት የሶሚሌ ክልል መስኖና ተፋሰስ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ ፈታ እንደገለጹት፤ በፕሮጀክቱ ከዋና የኤሌክትሪክ ማሰራጫ ጣቢያ በ180 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የወረዳው ህዝብ የዓመታት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ተመልሷል።
በዚህም የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
አቶ መሐመድ እንዳሉት ፕሮጀክቱ 5ሺህ 600 አባውራዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፀሐይ ብርሃን የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ማድረጉ በቀጣይ የወረዳውን ህዝብ ሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞ ዕውን ለማድረግ ያግዛል።
ሚኒ-ግሪድ ፕሮጀክቱ 75 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን ለቀጣይ 25 ዓመታት እንደሚያገለግልም ተመላክቷል።
በፕሮጀክቱ ምረቃ ላይ የተሳተፉት የማህበረሰቡ መሪ ዑጋዝ ፋራህ ሳህል እና የአገር ሽማግሌዎች የዘመናት የህዝብ ጥያቄ በመመለሱ ደስታቸው ወሰን እንደሌለው ገልጸዋል።