ቀጥታ፡

የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ዋና ጽሕፈት ቤት በአዲስ አበባ ይፋ የሚደረግበትን ቀን ምክንያት በማድረግ ዓለም አቀፍ የቦክስ ሻምፒዎና ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2016(ኢዜአ)፦የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ዋና ጽሕፈት ቤት በአዲስ አበባ ይፋ የሚደረግበትን ቀን ምክንያት በማድረግ ዓለም አቀፍ የቦክስ ሻምፒዎና ሊካሄድ ነው። 

የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ውድድሩ "አፍሪካ ዩናይት" በሚል መሪ ሃሳብ ነሐሴ 10 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ገልጿል።

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ የኢትዮጵያ ቦክስ በየጊዜው እድገት እያሳየ በአህጉርና ዓለም አቀፍ መድረኮች በውጤት መታጀብ ጀምሯል ብለዋል።

በተለይ የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት መቀመጫ ኢትዮጵያ መሆኗን ተከትሎ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ጽህፈት ቤቱ በአዲስ አበባ በይፋ እንደሚከፈት አስታውቀዋል፡፡

ይህም ኢትዮጵያ በአህጉር አቀፍ ደረጃ የአመራርነት ሚናዋ ዛሬም የጎላ መሆኑን ያሳያል ሲሉ ገልፀዋል።

የጽህፈት ቤቱ በአዲስ አበባ መከፈት ለሀገሪቱ የስፖርት ዕድገት መነቃቃት እንደሚፈጥር በማስታወቅ በተጨማሪም በሀገር ገፅታ ግንባታ እና በዲፕሎማሲው መስክ ትልቅ እምርታ ያመጣል ብለዋል።

የመገናኛ ብዙሃንም የጽሕፈት ቤቱን መከፈት እና የዓለም አቀፍ የቦክስ ውድድሩን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የኢትዮጵያ ገፅታን የሚገነቡ  ተግባሮችን እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርበዋል።

የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢያሱ ወሰን በበኩላቸው የኮንፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት በአዲስ አበባ መከፈቱ ኢትዮጵያ አህጉር አቀፍና ዓለማቀፍ ውድድሮችን እንድታስተናግድ ያግዛትል ሲሉ ገልፀዋል።

በዚህም ምክንያት በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ አዘጋጅነት ዓለምአቀፍ የቦክስ ሻምፒዮና እንደሚከናወን ተናግረዋል።

የዓለምአቀፉ ቦክስ አሶሴሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚስተር ክርስቶፈር ሮበርትስ ኢትዮጵያ የተሰጣትን ኃላፊነት በሚገባ እንደምትወጣ እምነት እንዳላቸውና ለዚህም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል።

ዓለምአቀፍ የቦክስ ሻምፒዮናው በስምንት የተለያዩ የኪሎግራም ምድቦች ተክፍሎ እንደሚካሄድ ተገልጿል። 

በሴቶች በ60 ኪ.ግ ሚሊየን ጨፎ ከኢትዮጵያ እና ሀድጅላ ከሊፍ ከአልጀሪያ የሚወዳደሩ ሲሆን በ54 ኪ.ግ ውድድር ደግሞ ውዳድ በርታል ከሞሮኮ እና ሳራ ሀግሂግሃት ጆ ከሴራሊዮን ይወዳደራሉ።

በ75 ኪ.ግ ፓትሪሺያ ምባታ ከናይጄሪያ እና ራዲ አዶንሲንዳ ግራማኒ ከሞዛምቢክ እንዲሁም በወንዶች 92 ኪ.ግ ፒተር አቡቲ ከኬኒያ እና አሎሬ አድማስ ከናይጄሪያ የሚወዳደሩ ይሆናል።

በ75 ኪ.ግ ደግሞ ያሲኔ ኢሎረዝ ከሞሮኮ እና ቲያንጎ ሙታንጋ ከሞዛምቢክ ይወዳደራሉ።

በ60 ኪ.ግ አቡበከር ሴፈን ከኢትዮጵያ እና ራሺድ ኦማሪ ከሶማሌያ ሲወዳዳሩ፤  በ80 ኪ.ግ ፒታ ካቤጂ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና የሱፍ ቻንጋላዊ ከታንዛኒያ የሚወዳደሩ ይሆናል።

በ51 ኪ.ግ ፓትሪክ ችንየምባ ከዛምቢያ እና ዴቪድ ፒና ከኬፕቨርዴ በውድድሩ እንደሚፋለሙ የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ካወጣው መርሐ ግብር መረዳት ተችሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም