በሀረሪ ክልል ከ2 ቢሊዮን 253 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በሀረሪ ክልል ከ2 ቢሊዮን 253 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2016(ኢዜአ)፦ በሀረሪ ክልል በ2016 የበጀት አመት ከ2 ቢሊዮን 253 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ሀላፊዋ ወይዘሮ ኢክራም አብዱልቃድር በክልሉ በ2016 የበጀት ከ2 ቢሊዮን 243 ሚሊዮን ለመሰብሰብ ታቅዶ 2 ቢሊዮን 253 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል ብለዋል።
ገቢው የተሰበሰበው ከቀጥታ ታክስ፣ ቀጥታ ካልሆነ የታክስ እና ታክስ ነክ ካልሆኑ ገቢዎች እንዲሁም ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢዎች መሆኑን ነው ያመላከቱት።
በዚህም ከተሰበሰበው ገቢ መካከልም 1 ቢሊዮን 285 ሚሊየን በላይ ከቀጥታ ታክስ፤ 542 ነጥብ 6 ሚሊዮን ቀጥታ ካልሆነ ታክስ፤ 64 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ታክስ ነክ ካልሆኑ ገቢዎች እንዲሁም 360 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ የተሰበሰበ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ለገቢው ማደግ በተለይም ከግብር አሰባሰብ ጋር በተያያዘ የአገልግሎት አሰጣጥ ስራዎችን ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
በቀጣይም የክልሉ ገቢን ለማጎልበት እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ መጠቆማቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳይች ቢሮ መረጃ ያመለክትል።