ቀጥታ፡

በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለፍራፍሬ ልማትና አገር በቀል እጽዋት ትኩረት በመስጠት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2016(ኢዜአ)፦በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለፍራፍሬ ልማትና ሀገር በቀል እጽዋት ትኩረት በመስጠት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ጋር በመሆን በጫካ ፕሮጀክት ሀገር በቀል የአረንጓዴ አሻራ ችግኞችን ተክለዋል። 


 

በመርሃ ግብሩም በባህር ዛፍ ተክል የተሸፈኑ ስፍራዎችን በአገር በቀል እጽዋቶች የመተካት ስራ ተከናውኗል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ጊዜ፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረ ወዲህ በኢትዮጵያ ያለው የደን ሽፋን መሻሻል ማሳየቱን አንስተዋል፡፡

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአገር አቀፍ ደረጃ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞችን የመትከል እቅድ ተይዞ ወደ ስራ መገባቱንም ነው ያብራሩት፡፡

በመርሃ-ግብሩም ለፍራፍሬ ልማትና አገር በቀል እጽዋት ትኩረት በመስጠት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአካባቢ መራቆትን ከመከላከል ባሻገር ለግብርና ምርታማነትና ቱሪዝም ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለውም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

በተለይ የአፈርና ውሃ ጥበቃን በማጎልበት ስንዴን ጨምሮ እንደ ሀገር የተያዙ የግብርና ኢኒሼቲቮችን ውጤታማ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል፡፡

እንደ ባህር ዛፍ ያሉና ከፍተኛ ውሃ የሚጠቀሙ ተክሎችን በሀገር በቀል እጽዋት መተካትም በመርሃ ግብሩ ትኩረት የተሰጠው ስራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ይህም በተለይ ከኢትዮጵያ አየር ጠባይ ጋር በተስማማ መልኩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራን ውጤታማ ለማድረግ እንደሚያግዝም ገልጸዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለሁለተኛ ጊዜ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ማከናወናቸውም ነው የተገለጸው፡፡
 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም