ቀጥታ፡

ለአገራዊ የምጣኔ ኃብት ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ውጤታማነት የሚቀርቡ ሳይንሳዊ ምክረ ኃሳቦች ተጠናክረው ይቀጥላሉ   

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2016(ኢዜአ)፦ ለአገራዊ የምጣኔ ኃብት ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ውጤታማነት የሚቀርቡ ሳይንሳዊ ምክረ ኃሳቦች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር ገለጸ።  

ማኅበሩ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የሚመክረውን 21ኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል።

የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ መንግሥት በአገሪቱ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ እንዲኖር ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያከናወነ ነው።

በተለይም የዋጋ ንረት ለመቀነስ፣ ዘላቂ ልማት ለማምጣትና ሌሎች አገራዊ የልማት እቅዶች ላይ እያከናወነ ያለውን ተግባር በጥናትና ምርምር ምክረ ኃሳቦች መደገፍ ይገባል ብለዋል።

በተጨማሪም  ኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገች ላለው የአገር በቀል ምጣኔ ኃብት መርኃ ግብርና የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድ መሳካት የምሁራን ሚና ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። 

በዚህ ረገድ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎችና ከሌሎች የሙያ ማኅበራት ጋር በመተባበር የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት ለማ ጉዲሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ማኅበሩ አገራዊ የሆነ የምጣኔ ኃብት እድገት ለማምጣት የሚያግዙ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ምክረ ኃሳቦችን  እያቀረበ ይገኛል ብለዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያ እየተገበረቻቸው ላሉ የምጣኔ ኃብት ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ውጤታማነት ሳይንሳዊ ምክረ ኃሳቦችን ማቅረቡን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ጉባኤ የማኅበሩ አባላት፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ  ድርጅቶችና ሌሎች ተሳታፊዎች ታድመዋል።

በጉባኤው የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያን ጨምሮ ሌሎች የምጣኔ ኃብት ጉዳዮች ላይ የፓናል ውይይቶች ይደረጋሉ ተብሏል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም