በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመጪው ሣምንት ለሀገራዊ ምክክር አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ ይጀመራል - ኮሚሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመጪው ሣምንት ለሀገራዊ ምክክር አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ ይጀመራል - ኮሚሽኑ
አሶሳ፣ ሐምሌ 12 /2016(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመጪው ሣምንት አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ እንደሚጀምር አስታወቀ።
ኮሚሽኑ በክልሉ ከሚሰሩ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጋር ዛሬ ተወያይቷል።
በኮሚሽኑ የክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮች እና የዳያስፓራ አስተባባሪ አቶ ረታ ጌራ እንደገለጹት ኮሚሽኑ በክልሉ ከመጪው ረቡዕ ጀምሮ ለሰባት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራ ያከናውናል።
በዚህ ሂደትም በየቀኑ እስከ 1 ሺህ 200 የሚበልጡ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉባቸው መድረኮች እንደሚካሄዱ ተናግረዋል።
በመድረኮቹ ከ10 በላይ የተለያዩ የማህበረሰብ ከፍሎች እንደሚወከሉ ያስረዱት አስተባባሪው፣ ከነዚህም ታዋቂ ግለሰቦች፣ ሀገር አቀፍና ክልል አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራት ተወካዮች ይገኙበታል ብለዋል።
አጀንዳ የማሰባሰቡ ሥራን ስኬታማ ለማድረግ መገናኛ ብዙሃን ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በኮሚሽኑ የተደራሽና አጋርነት ባለሙያ አቶ ፍሬሰናይ ገበየሁ መገናኛ ብዙሃን አጀንዳ የማሰባሰቡ ስራ ስኬታማነት ዋና ዋና የድርጊት መርሃ ግብሮች ተለይተው መቀመጣቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ የአጀንዳ አሰባሰቡን ሥራ ሀገር አቀፍ እና ክልል አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት እንደሚዘግቡት አስታውቀዋል።