ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል በመኸር እርሻ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ ለማሳካት እየተሰራ ነው

ጋምቤላ፣ ሐምሌ 12/2016 (ኢዜአ)፡-በጋምቤላ ክልል በተያዘው የመኸር እርሻ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ በዘንድሮው የመኸር እርሻ ለማልማት ከታቀደው መሬት ከ85 ከመቶ በላይ የሚሆነው በዘር መሸፈኑም ተገልጿል።


 

የጋምቤላ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ሉዋል ለኢዜአ እንደገለጹት በዘንድሮው የመኸር እርሻ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና እንደ ሀገር ከተረጂነት ለመላቀቅ የታለመውን ግብ ለማሳካት ጥረት እየተደረገ ነው።

በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የእርሻ ትራክተሮችን በማሰማራትና የግብርና ግብዓቶችን በማሰራጨት የመኸር እርሻውን ውጤታማ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በመኸር እርሻ ለማልማት ከታቀደው ከ164 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ እስካሁን ከ141ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበቆሎ፣ ማሽላ፣ ሰሊጥ፣ ለውዝና በሌሎች የሰብልና የጓሮ አትክልቶች መሸፈኑን አስረድተዋል።

በዘር ከተሸፈነው መካከል ከ54 ሺህ ሄክታር የሚበልጠው መሬት በቆሎን ጨምሮ በተመረጡ የሰብል ዓይነቶች በኩታ ገጠም እየለማ መሆኑን በማከል።

እንደ አቶ ኡጁሉ ገለጻ ቀሪውን በዘር ያልተሸፈነ ከ23 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት ዘግይተው በሚዘሩ የሩዝ፣ የማሾ፣ የስንዴና ሌሎች የሰብልና የጓሮ አትክልቶች ለማልማት ብርቱ ጥረት እየተደገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በክልሉ በመኸር እርሻ እየለማ ካለው መሬትም ከ5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሰብልና የጓሮ አትክልት ምርት ለመሰብሰብ ግብ መጣሉን ጠቁመው፤ ይህም ከባለፈው ዓመት በ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።

ቢሮው ከአዲሱ በጀት ዓመት ጀምሮ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ክልሉ በማስገባትና የግብርና ግብዓቶችን ሙሉ ለሙሉ በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ ከግብርና ሚኒስትር ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ ለተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅትም ትኩረት መሰጠቱን ነው የገለጹት። 


 

በአበቦ ወረዳ የመንደር 14 ቀበሌ ነዋሪ ወጣት አርሶ አደር ኡኩኝ ኦኬሎ በበኩሉ፤ የግብርና ምርታማነቱን ለማሳደግ ቀደም ሲል ይለሙ ያልነበሩ መሬቶችን ጭምር በመጠቀም የእርሻ ስራውን እያከናወነ መሆኑን ገልጿል።

 

በዘንድሮው ዓመት ሁለት ሄክታር የሚጠጋ መሬት በበቆሎ ሰብል ማልማቱን የጠቀሰው ወጣቱ አርሶ አደር እየለማ ያለው በቆሎ ከራሱ ፍጆታ አልፎ ለገበያም እንደሚተርፍ ገልጿል።

የዘንድሮው የዝናብ ስርጭት ከቀዳሚዎቹ ዓመታት የተሻለና ለግብርና ስራ ምቹ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በዚሁ ወረዳ የመንደር 13 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ኢብራሂም በሽር ናቸው።


 

በማዳበሪያና በፀረ- አረም ኬሚካል አጠቃቀም  የባለሙያዎችና የመንግስት እገዛ ሊጠናከር ይገባልም ብለዋል።

በክልሉ ከ2017 በጀት ዓመት ጀምሮ ማዳበሪያን ጨምሮ ሌሎች የግብርና ግብዓቶች ለአርሶ አደሩና ለባለሃብቶች ለማቅረብ  መታቀዱን ቢሮው ገልጿል።  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም