ቀጥታ፡

በተደጋጋሚ የሚከሰት የመብራት መጥፋት በእለት ተለት ኢኮኖሚያዊ ና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎቻችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል-ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2016(ኢዜአ)፦ በተደጋጋሚ የሚከሰት የመብራት መጥፋት በእለት ተለት ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎቻችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል ሲሉ የመዲናዋ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበኩሉ የነዋሪዎችን ቅሬታ የሚፈቱ ቴክኖለጂዎችን በሚቀጥለው ዓመት አጋማሽ ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራሁ ነው ብሏል፡፡

ነዋሪዎቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፤ ለተከታታይ ቀናት ያለመብራት በጨለማ የሚቆዩበት ጊዜ በርካታ ነው፡፡

ቅሬታቸውን ካቀረቡ የመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ የሺ መለሰ፤ የሰዎች የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ አብዛኛው ከመብራት ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ይሁን እንጂ በተለያዩ ምክንያቶች በተደጋጋሚ መብራት እንደሚጠፋ እና ፈጣን ምላሽ እንደማይሰጥ በመጥቀስ ባለሙያዎች ቀናትን አሳልፈው በመምጣት ችግሩን አስተካክለው እንደሄዱ ብዙም ሳይቆይ መብራት ወዲያው የሚጠፋበት አግባብ መኖሩን ነው የተናገሩት፡፡ 

ይህም በእለት ተለት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴያቸው ላይ እንቅፋት እንደሆነባቸው ነው የገለጹት፡፡ 

ሌላኛዋ ቅሬታ አቅራቢ ወይዘሮ ትዕግስት ተዋበ በበኩላቸው፤ መብራት ጠፍቶ በሚመጣበት ወቅት የኤሌክትሪክ እቃዎችን እያቃጠለባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 


 

"መብራት ሲጠፋ ጠፋ ብለን ለማሳወቅ ስንደውል በአብዛኛው ስልክ አይነሳም፤ አንዳንዴ ቢነሳም ፈጥነው ምላሽ አይሰጡም " በዚህ ምክንያት ለበርካታ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮች ተጋልጠናል ነው ያሉት፡፡

ወይዘሮ ትዕግስት ተዋበ አክለውም፤ ቆጣሪ በትክክል እንደማይነበብላቸው እና ለተጋነነ የኤሌክትሪክ ክፍያ እየተዳረጉ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ወይዘሮ ጸሐይ ገብሬ፤ የተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ቢመጣም ከቆጣሪ ንባብ ጋር ተያይዞ አሁንም ችግሮች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡

በዚህም ምክንያት የተጋነነ ወርሃዊ የኤሌክትሪክ ክፍያ እየተጠየቁ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የመብራት መቆራረጥ ከድሮው የተሻለ ቢሆንም አሁንም መሻሻል ያለባቸው በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ ተስፋዬ ተሰማ ናቸው፡፡


 

መብራት በሚጠፋበት ወቅት ፍሪጅ የሚያስፈልጋቸው የምግብ አይነቶች ለብልሽት እየተዳረጉ መሆኑን በመጥቀስ ለተቋሙ ብንደውልም በፍጥነት መጥተው የማስተካከል ልምዳቸው ዝቅተኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገበየሁ ሊካሳ (ደ/ር) በነዋሪዎች የተነሱ ቅሬታዎች በአመዛኙ ተገቢነት እንዳላቸው ተናግረዋል ፡፡


 

የኅብረተሰቡ የኤሌክትሪክ ፍላጎት እየጨመረ መሆኑን ተከትሎ ይህንኑ በሚመጥን ሁኔታ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮችንና ትራስፎርመሮችን ማሳደግ አለመቻሉ ለችግሮቹ መንስኤ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አዲስ አበባን በሚመጥን ልክ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለመስጠት ባለፉት ጊዜያት ከተለያዩ ረጂ ተቋማት በተገኘ ገንዘብ የተለያዩ የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማቶች ማስፋፊያ ስራ ሲከናወን መቆየቱን አንስተዋል፡፡

ከማስፋፊያና በአዲስ ከመቀየር ሥራዎች ጎን ለጎን በተለይ መብራት ሲጠፋ ከቢሮ ሆኖ የጠፋበትን ሥፍራ በቀላሉ ለማወቅ የሚያስችል " ስካዳ "  የተባለ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ለማዋል ሥራዎች መጀመራቸውን ገልፀዋል፡፡

ይህም ከነዋሪዎች የሚነሳውን መብራት ሲጠፋ ቶሎ ምላሽ አይሰጠንም የሚለውን ቅሬታ ሙሉ ለሙሉ የሚፈታ ይሆናል ነው ያሉት፡፡ 

ከቆጣሪ ንባብ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት የሚያግዙ ስራዎች መጀመራቸውንም አስታውቀዋል፡፡

እንዲሁም ደንበኞች ክፍያ ለመፈጸም ወይም ካርድ ለመሙላት ወደ ቢሮ መምጣት ሳይጠበቅባቸው እንደ ሞባይል ካርድ ሱቅ ላይ በመግዛት አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት አሠራር እየተዘረጋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለዚህ የሚሆኑ ቴክኖሎጂዎች ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በመግባት ላይ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም